መጋቢት 28/2018 - ዓለም አቀፍ ወሬዎች
- 1 hour ago
- 2 min read
የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት (ሐማስ) የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚፈፀመውን ጥቃት አቁሞ ጠቅልሎ ካልወጣ በስተቀር በጭራሽ ትጥቅ አልፈታም አለ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዛ ሰርጥ የወደፊት ሰላም ቀደም ሲል ያቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች የሰላም እቅድ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ የሚጠይቅ መሆኑን ሬውተርስ አስታውሷል፡፡

የሐማስ የበላዮች በዚህ ጉዳይ ትናንት ከአደራዳሪዎቹ ጋር መመካከራቸው ተሰምቷል፡፡
ይሄን ተከትሎም የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ ቃል አቀባይ አቡ ኦባይዳ የእስራኤል ጦር ከመንፈቅ በፊት በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት የጋዛ ሰርጥን ለቅቆ ካልወጣ በስተቀር በጭራሽ ትጥቅ አንፈታም ብለዋል፡፡
በጋዛ የወደፊት ዘላቂ ስለማለቱ የሐማስ ትጥቅ መፍታት ነገር በጣሙን አስቸጋሪው ጉዳይ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሐማስ ትጥቅ አልፈታም በማለቱ ጉዳይ ከእስራኤል በኩል ለጊዜው የተሰጠ ፈጣን አስተያየት እንደሌለ ተጠቅሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢራን ያስቀመጡት አዲስ የ48 ሰዓታት የማስጠንቀቂያ የጊዜ ገደብ ሲያበቃ የሚያደርጉ የሚፈፅሙትን የጦር ተግባር እወቁልኝ አሉ፡፡
የጊዜ ገደቡ ነገ ያበቃል፡፡
ትራምፕ ለኢራን የተሰጣት የጊዜ ገደብ እንዳበቃ ሁሉም የኤሌክትሪክ አውታሮቿ ይመታሉ ማለታቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የአገሪቱን ድልድዮች ሁሉ እናፈራርሳቸዋለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት በኢራን ላይ ዛቻቸውን በቀነ ገደብ ቀንብበው ያሰሙት ኢራን የምትባለውን ለመፈፀም ያለ አንዳች ማንገራገር እንድትስማማ እና የሆርሙዝን ሰርጥ እንድትከፍት ለማስገደድ አልመው ነው፡፡
ከጦርነቱ በፊት በሆርሙዝ ሰርጥ በየወሩ 3 ሺህ ያህል የንግድ መርከቦች ሲመላለሱበት ነበር፡፡
ከጦርነቱ መቀስቀስ ወዲህ በባህር መተላለፊያው የሚቀዝፉ መርከቦች ብዛት በእጅጉ መቀነሱ ይነገራል፡፡
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ ክፍሎች የኩፉኝ ወረርሽኝ እየተዛመተ ነው ተባለ፡፡
በሽታው በግዛቱ ሶስት ስፍራዎች እየተዛመተ መሆኑን ሬዲዮ ዳባንጋ በድረ ገጹ ፅፏል፡፡
ብዛታቸው በአሃዝ ይሄን ያህል ነው ተብሎ ባይጠቀስም በበሽታው የሞቱ ሰዎች አሉ ተብሏል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል አለም አቀፍ እና አገር በቀል የረድኤት ድርጅቶች እንዲረባረቡ ተጠይቋል፡፡
ሱዳን በመንግስት ጦር እና በRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል በሚካሄድ ጦርነት ውስጥ ነች፡፡
ዳርፉር ደግሞ ከተፋላዎቹ የውጊያ አውድማዎች አንዷ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
በባንግላዴሽ ኩፍኝ እንደሆነ የተጠረጠረ ወረርሽኝ 100 ያህል ህፃናትን ገደለ ተባለ፡፡
ከ6 ሺህ 400 በላይ ሕፃናት የኩፍኝ በሽታ ምልክት እንደታየባቸው AFP ፅፏል፡፡
በወረርሽኙ የሞቱት አብዛኞቹ እድሜያቸው ከመንፈቅ በታች የሆነ ሕፃናት መሆናቸው ታውቋል፡፡
ቀደም ሲል በቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሐሲና አስተዳደር ተቀስቅሶ በነበረው ሕዝባዊ እምቢታ ምክንያት የክትባት ክንውኑ መቋረጡ ለአሁኑ ወረርሽኝ መቀስቀስ በምክንያትነት ቀርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት የወረርሽኝ መስፋፋት በተስተዋለባቸው 30 ስፍራዎች ክትባት መስጠት ተጀምሯል ተብሏል፡፡
በሽታው በማሳል እና በማስነጠስ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በአለም የጤና ድርጅት በተጠናከረ አሃዝ መሰረት ኩፍኝ በአለም ዙሪያ በየአመቱ 95 ሺህ ያህል ሰዎችን እንደሚገድል መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments