top of page

የዓለም ጤና ድርጅት ለካላ-አዛር ሕመም አዲስና አጭር የሕክምና መመሪያ ይፋ ማድረጉ ተሰማ፡፡

  • 1 hour ago
  • 2 min read

ሐምሌ 24 2018


የዓለም ጤና ድርጅት ለካላ-አዛር ሕመም አዲስና አጭር የሕክምና መመሪያ ይፋ ማድረጉ ተሰማ፡፡



የካላ-አዛር ሕመም በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፍ፣ የውስጥ አካላትን የሚጎዳ እና በወቅቱ ሕክምና ካልተደረገለት ገዳይ ሊሆን የሚችል ከባድ የጤና ችግር ነው።


በሽታው ከፍተኛ ትኩሳት፣ የክብደት መቀነስ፣ የደም ማነስ፣ እንዲሁም የጣፊያ እና የጉበት ማብጥ የሚያስከትል ነው።


በአሁኑ ወቅት ካላ-አዛር በ80 በሚጠጉ ሀገራት በወረርሽኝ መልክ የሚገኝ ሲሆን፣ በየዓመቱ ከ50,000 እስከ 90,000 የሚደርሱ አዳዲስ ታካሚዎች ይመዘገባሉ።


በተለይም ምስራቅ አፍሪካ የበሽታውን ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ጫና የምትሸከም ቀጠና ስትሆን፣ እ.ኤ.አ በ2024 ከተመዘገቡት በሽተኞች መካከል 79 በመቶ የሚሆኑት የዚሁ ቀጠና ናቸው።


ኢትዮጵያም በሽታው አሁንም ከፍተኛ የሕዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ከቀጠለባቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንዷ ናት።


ይህንን ለመግታትና ታካሚዎችን ከረጅም ጊዜ እንግልት ለማዳን፣ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ለአጭር ጊዜ የሚወስዱና ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ናቸው ያለቸውን አዳዲስ የሕክምና ፕሮቶኮሎችን ይፋ ማድረጉ ተሰምቷል።


መመሪያው ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ፣ ረጅም ጊዜ የሚወስዱና ከፍተኛ ሕመም የሚያስከትሉ የመርፌ ሕክምናዎችን በአፍ በሚወሰዱ መድኃኒቶች በተደገፉና ለታካሚ ምቹ በሆኑ አማራጮች የሚተካ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡


ታካሚዎች በሆስፒታል የሚያሳልፉት ከ60 እስከ 90 ቀናት የነበረው ጊዜ ወደ 14 ቀናት ብቻ እንዲያጥር ተደርጓልም ተብሏል።


በአዲሱ ፕሮቶኮል መሰረት ቀደም ሲል በ17 ቀናት ውስጥ ይሰጡ የነበሩ 34 መርፌዎች ወደ 14 ቀናት እና 14 መርፌዎች (በቀን አንድ መርፌ) ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል።


በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካላት አፌዝ ምርምር እና ሕክምና ማዕከል ባልደረባ ዶ/ር እሌኒ አየለ፣ የተሻሻለው መመሪያ ለኢትዮጵያ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።


"በኢትዮጵያ በርካታ የአካላት አፌዝ ታካሚዎቻችን ዘግይተው እና በጣም ታመው የሚመጡ አዋቂዎች ናቸው፤ ከፊሎቹ ደግሞ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሕመም አለባቸው" ያሉት ዶ/ር እሌኒ፣ አጫጭር እና መርዛማነታቸው አነስተኛ የሆኑ ሕክምናዎች የታካሚዎችን የመዳን እድል ለማሻሻል ብቻ ሳይሆን፣ ሕክምናቸውን በአግባቡ ጨርሰው በፍጥነት ወደ መደበኛ የሥራ እና ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።


የዓለም የጤና ድርጅት የወባ እና ችላ የተባሉ ሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል ንጋሚጄ ማዳንዲ በበኩላቸው፣ አዲሱ መመሪያ በሽታውን በመዋጋት ረገድ ትልቅ ድርሻ አንደሚኖረው ተናግረው ፣ "ወደፊትም የበለጠ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ አጭር እና ለታካሚ ምቹ የሆኑ የሕክምና ዘዴዎችን በመመከር ይህንን አጥፊ በሽታ ጨርሶ ለማጥፋት የሚደረገውን ጉዞ እናፋጥናለን" ብለዋል።


ንጋቱ ሙሉ

Recent Posts

See All
የሐምሌ 24 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ኮንጎ በኮንጎ ኪንሻሣ በኢቦላ የሚያዙ ሕሙማንና ወረርሽኙ የሚገድላቸው ሰዎች ብዛት በጣሙን እየጨመረ ነው ተባለ፡፡ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠው ሰዎች ብዛት ከ3 ሺህ 400 መብለጡን አናዶሉ ፅፏል፡፡ ወረርሽኙ የገደላቸው ሰዎች ብዛት ከ1 ሺህ 500 በላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡ በአገሪቱ በኢቦላ በሽታ የሚያዙ ሰዎች

 
 
 
በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱን ታሪክ ብቻ ለይቶና አጉልቶ የሚያቀርብበት ስርዐት መቀየር እንዳለበት የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ ።

ሐምሌ 23 2018 በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱን ታሪክ ብቻ ለይቶና አጉልቶ የሚያቀርብበት ስርዐት መቀየር እንዳለበት የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ ። በኢትዮጵያ የብሄረሰቦች ታሪክ ጥልቅ ትስስር እና መስተጋብር ያለው ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሞያዎች ማህበር ከላይፍ ኤንድ ፒስ ኢንስ

 
 
 
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page