top of page

የሐምሌ 24 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

  • 55 minutes ago
  • 2 min read


በኮንጎ ኪንሻሣ በኢቦላ የሚያዙ ሕሙማንና ወረርሽኙ የሚገድላቸው ሰዎች ብዛት በጣሙን እየጨመረ ነው ተባለ፡፡


በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠው ሰዎች ብዛት ከ3 ሺህ 400 መብለጡን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ወረርሽኙ የገደላቸው ሰዎች ብዛት ከ1 ሺህ 500 በላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡


በአገሪቱ በኢቦላ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ብዛት በየ20 ቀኑ በእጥፍ እያደገ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡


ወረርሽኙ የመግደል አቅም ከ44 በመቶ በላይ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


ወረርሽኙ ወደ አዳዲስ ስፍራዎችም በመዛመት ላይ ነው ተብሏል፡፡


በኮንጎ ኪንሻሣ ኢቦላ በወረርሽኝ ደረጃ መቀስቀሱ ከተነገረ ወደ 3ኛ ወሩ ተቃርቧል፡፡



ከ130 በላይ የዮርዳኖስ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአሜሪካ ጦር ከአገሪቱ እንዲወጣላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡


ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ቀደም ሲል ከአሜሪካ ጋር የተደረሱ ወታደራዊ እና የጦር ትብብር ስምምነቶችም ከነአካቴው እንዲሰረዙ መጠየቃቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


ጥያቄውን ያቀረቡት ታዋቂ ፖለቲከኞች ምሁራን እና የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡


ፊርማቸው ያረፈበትን የጥያቄ ማቅረቢያ ደብዳቤ ለመንግስት እንዳስገቡ ተጠቅሷል፡፡


ዮርዳኖስ ከኢራን የአፀፋ ጥቃት ሰለባ የአካባቢው አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡


በተለይም ከቅርብ ሳምንት ወዲህ ዮርዳኖስ የኢራን የአፀፋ ጥቃት ሰለባነቷ መባባሱ ይነገራል፡፡


ዮርዳኖሳውያኑ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአገሪቱ መንግስት ለተሟላ የአገሪቱ ሉአላዊነት መረጋገጥ ሊሰራ ይገባዋል ብለዋል በጥያቄያቸው፡፡


በዚህ ረገድ የዮርዳኖስ መንግስት የፈጠነ ምላሽ እና የአሜሪካ አስተያየት አልተሰማም፡፡




የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት /ሐማስ/ ትጥቅ የምፈታው የእስራኤል ሀይሎች ከጋዛ ሰርጥ ሙሉ በሙሉ ለቅቀው ሲወጡ ብቻ ነው አለ፡፡


የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሰርጥ ጠቅልሎ ካልወጣ በስተቀር በጭራሽ ትጥቅ አንፈታም ያሉት የሐማስ የተደራዳሪዎች ቡድን አባል ጋዚ ሐማድ እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡


የጋዚ ሐማድ አስተያየት የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ ስምምነት ተደርሷል ማለታቸው ተከትሎ ነው፡፡


ትራምፕ ሌሎች የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖችም ትጥቅ ፍትተው የጋዛን ፀጥታ የማስከበሩን ሀላፊነት አዲሱ የፍልስጤማውያን የፖሊስ ሀይል እንደሚረከብ ተናግረዋል፡፡


አለም አቀፍ አረጋጊ ሀይልም በሰርጡ እንደሚሰማራ ታውቋል፡፡


ሐማስ ግን ትጥቅ የምፈታው የእስራኤል ሀይሎች ሙሉ በሙሉ ከሰርጡ ለቅቀው ሲወጡ ብቻ ነው የሚል የስምምነት ትርጓሜ ይዞ መጥቷል፡፡


ሐማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ትጥቅ ለመፍታት እንዲስማሙ ግብፅ ፣ ካታር እና ቱርክ የአደራዳሪነት ሚና እንደነበራቸው መረጃው አስታውሷል፡፡



ኢራን እና አሜሪካ በጦር መጠቃቃታቸውን በቀጠሉበት አጋጣሚም ቢሆን በድርድር ላይ መሆናቸውን የፓኪስታን ሹሞች ተናገሩ፡፡


ፓኪስታን በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ሲካሄድ በቆየው የሰላም ንግግር ስሟ በዋና አደራዳሪነት ሲነሳ መቆየቱን AFP ፅፏል፡፡


ኢራን በዮርዳኖስ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር ተቋም ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ የሁለቱ አገሮች በጦር መጠቃቃት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡


የአሜሪካ እና የኢራን የአሁኑ ድርድር የሆርሙዝ የባህር መተላለፊያ ወሽመጥን ውጥረት ለማርገብ የታለመ እንደሆነ የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሹሞች ተናግረዋል፡፡


ድርድሩ ቀጥተኛ ይሁን ፤ አይሁን በግልጽ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡


ሁለቱ አገሮች ቀደም ሲል ለጦርነቱ ማስቆሚያ የመግባቢያ ስምምነት ከፈረሙ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ ከፍተኛ እልህ እየተጋቡ ነው፡፡


ትናንት እንኳ አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማለፍ የሞከሩ የጭነት መርከቦች ወደመጡበት እንዲመለሱ አስገድጃለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱን ታሪክ ብቻ ለይቶና አጉልቶ የሚያቀርብበት ስርዐት መቀየር እንዳለበት የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ ።

ሐምሌ 23 2018 በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱን ታሪክ ብቻ ለይቶና አጉልቶ የሚያቀርብበት ስርዐት መቀየር እንዳለበት የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ ። በኢትዮጵያ የብሄረሰቦች ታሪክ ጥልቅ ትስስር እና መስተጋብር ያለው ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሞያዎች ማህበር ከላይፍ ኤንድ ፒስ ኢንስ

 
 
 
በ2018 በጀት ዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ሐምሌ 23 2018 በ2018 በጀት ዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በየዓመቱ በሀገሪቱ የሚገኘው የምርት መጠን እያደገ እንደሚመጣ ሪፖርቶች ያመልክታሉ። በገበያው ውስጥ ግን የምርት ዋጋ ከአመት አመት እየጨመረ እንጂ ሲቀንስም አይታይም። ይህ ለምን ሆነ? እውነትስ

 
 
 
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page