top of page

መጋቢት 12፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

የደቡብ ሱዳኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ሪያክ ማቻር በምርጫው ጉዳይ ባለ ድርሻ አካላት አደራዳሪዎች ባሉበት ልንመክርበት ይገባል አሉ፡፡


ከ6 አመታት በፊት የተደረሰው 2ኛው አጠቃላይ የሰላም ስምምነት በአገሪቱ ምርጫ እንዲካሄድ ይጠይቃል፡፡


ምርጫው በመጪው አመት ታህሳስ ወር እንዲካሄድ መታቀዱ ይነገራል፡፡


ከሰላም ስምምነቱ እስካሁን ተፈፃሚ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ ይባላል፡፡


ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ደግሞ በስምምነቱ አፈፃፀም ረገድ አጋጥመዋል የተባሉ ችግሮች ከወዲሁ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ማቻር በመግለጫ ጠይቀዋል፡፡


ደቡብ ሱዳን እስከ ስምምነቱ ድረስ ከ5 አመታ በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ማሳለፏን ዘ ኢስት አፍሪካን ፅፏል፡፡




የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ የባንክ ሂሳብ በከፊል እንዳይንቀሳቀስ ታገደ፡፡


የዙማ የባንክ ሒሳብ በከፊል እንዳይቀሳቀስ የታገደው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደሆነ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡


ጉዳዩ በፕሬዘዳንትነታቸው ወቅት በንካንድላ የሚገኘውን የግል መኖሪያ ቤታቸውን ከመንግስት ካዝና በወጣ ገንዘብ አስጊጠዋል ከመባሉ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ታውቋል፡፡


የዙማ የባንክ ሂሳብ በከፊል እንዳይንቀሳቀስ የታገደው አገሪቱ ወደ ምርጫ በተቃረበችበት ወቅት እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡


የቀድሞው ፕሬዘዳንት KM የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ማህበር ማደራጀታቸው ይነገራል፡፡


KM ደግሞ በዘር መድልኦው ዘመን የአሁኑ ገዢ የፖለቲካ ማህበር ANC ወታደራዊ ክንፍ መጠሪያ ነበር፡፡


ጉዳዩ እያወዛገበ ነው የተባለ ሲሆን ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ አይቀርም ተብሏል፡፡



በዚምባብዌ የማዕድን ባለንብረቶች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንቷ በማጭበረበር ወንጀል ዘብጥያ ወረዱ፡፡


ሔነሪታ ሩሻዋያ የተባሉት የማዕድን ባለንብረቶቹ ፌዴሬሽን የበላይዋ ለእስር የተዳረጉት ንብረታቸው ያልሆነውን የማዕድን ስፍራ ለመሸጥ ሞክረዋል ተብለው እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ሴትዮዋ ትናንት ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል፡፡


አቃቢያነ ህግ ሩሻዋያ የዋስትና መብት እንዲነፈጋቸው መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡


ከ4 አመታት በፊትም ከ300 ሺህ ዶላር በላይ የዋጋ ግምት ያለው ወርቅ በኮንትሮባንድ ከአገር ለማስወጣት ሲሞክሩ ተይዘው በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እንደተባሉ ዘገባው አስታውሷል፡፡


ሴቲዮዋ በወርቅ ኮንትሮባንድ ስማቸው በክፉ ሲነሳ መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የፓኪስታን ጦር በግዋዳር ወደብ ላይ ድንገት ደራሽ ጥቃት የሰነዘሩ 8 ታጣቂዎችን በሙሉ ገደልኳቸው አለ፡፡


ወደቡ በአገሪቱ ደቡባዊ ምዕራብ ክፍል የሚገኝ እና በቻይናውያን የገንዘብ እና የሙያ ድጋፍ የተገነባ እንደሆነ ABC ፅፏል፡፡


በዚያ የነበሩ ቻይናውያን አንዳችም ክፉ አላገኛቸውም ተብሏል፡፡


ጥቃት አድራሾቹ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ እና የመገንጠል አቀንቃኞች እንደሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


የፓኪስታን ጦር ጥቃት አድራሾቹን በሙሉ ጨርሻቸዋለሁ ቢልም ከራሱ ወገን ስለደረሰው ጉዳት ግን ያነሳው ነገር የለም፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




bottom of page