top of page

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የአየር እና የባህር ሀይሎች እንዳልነበሩ አድርገን አውድመናቸዋል አሉ፡፡

  • Mar 4
  • 2 min read

የካቲት 25/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

 

 

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የአየር እና የባህር ሀይሎች እንዳልነበሩ አድርገን አውድመናቸዋል አሉ፡፡

 

ትራምፕ የኢራንን የአየር እና የባህር ሀይሎች እንዳልነበሩ አድርገን ደምስሰናቸዋል ያሉት በዋይት ሐውስ ከጀርመኑ መራሄ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርዝ ጋር ከተመካከሩ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ኢራን የባህር እና የአየር ሀይል እንዳይኖራት ማድረጋቸው ትራምፕ ተናግረዋል፡፡

 

አሜሪካ እና እስራኤል ካለፈው ሳምንት ቅዳሜ አንስቶ በጣምራ በኢራን ላይ ከባድ ድብደባ እየፈፀሙ ነው፡፡

 

ቢቢሲ እንደፃፈው ትራምፕ የኢራንን የጦር አቅም አነካክቼዋለሁ ቢሉም ፋርሳዊቱ አገር በእስራኤል እና በቀጠናው በሚገኙ የአሜሪካ ተቋሞች ላይ የአፀፋ ጥቃቷን እንደቀጠለች ነው፡፡

 

ኢራን በሰነዘረችው የሰው አልባ በራሪ አካል ድሮን ጥቃት በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ዱባይ የሚገኘው የአሜሪካ የቆንስላ ፅህፈት ቤት በእሳት ተያይዟል ተብሏል፡፡

 

በቆንስላ ፅህፈት ቤቱ ላይ የተቀሰቀሰው ቃጠሎ ጠፍቷል መባሉ ተሰምቷል፡፡

 

በሳውዲ አረቢያ ሪያድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም በኢራን የድሮን ድብደባ ቃጠሎ ገጥሞታል ተብሏል፡፡

 

 

ሳውዲ አረቢያ በኢራን ተሰንዝሮብኛል ላለችው ጥቃት ምላሽ መስጠቴ አይቀርም አለች፡፡

 

የባህረ ሰላጤዋ ቱጃር አገር ራሴን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ አደርጋለሁ ማለቷን ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

ሳውዲ አረቢያ ለኢራን ጥቃት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን እወቁልኝ ያለው የአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡

 

የካታር መንግስት ደግሞ ኢራን ለስለላ ያሰማራቻቸው ናቸው ያላቸውን 10 ተጠርጣሪዎች ይዤ አስሬያለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡

 

በስለላ ተጠርጥረው የተያዙት 10 ግለሰቦች አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል የውጭ ተልዕኮ አባላት ናቸው ተብሏል፡፡

 

ከመካከላቸው ሰባቱ የስለላ ተልዕኮ እንደነበራቸው ተጠቅሷል፡፡

 

የተቀሩት ሶስቱ ደግሞ የሰው አልባ በራሪ አካል /ድሮን/ ዝወራ ስልጠና ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡

 

በዚህ ጉዳይ የኢራን አስተያየት ምን እንደሆነ አልተጠቀሰም፡፡

 

 

በሶማሊያ እየተባባሰ የመጣው ድርቅ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ለከፋ ረሃብ እንደሚዳርግ አለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስጠነቀቀ፡፡

 

ድርቁ በበረታባቸው ግዛቶች እንስሳትን እየጨረሰ መሆኑን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

በተለይም ጋልሙዱግ የተባለችዋ ግዛት ድርቁ የጠናባት ነች ተብሏል፡፡

 

እንደ ግመል እና ፍየል ያሉ እንስሳትን እየጨረሰ ያለው ድርቅ ወደ ሰዎችም እንዳይሸጋገር አስግቷል ተብሏል፡፡

 

አለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በገጠገመው የገንዘብ ችግር ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱን መቀነሱ ተሰምቷል፡፡

 

የሶማሊያ መንግስት ጦር እንደ አልሸባብ እና I.S.I.S ካሉ ፅንፈኞች ጋር ሲዋጋ በርካታ አመታትን አስቆጥሯል፡፡

 

በዚያ ላይ አገሪቱን የሚደጋግማት ድርቅ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነባት በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

 

 

አሜሪካ በሩዋንዳ ጦር ሀይል እና በ4 ከፍተኛ አዛዦቹ ላይ ማዕቀብ ጣለችባቸው፡፡

 

ታላቋ አገር በሩዋንዳ ጦር ሀይል እና በ4 ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ ላይ ማዕቀብ የጣለችባቸው በጎረቤት ኮንጎ ኪንሻሣ የቀጠለው ግጭት እያባባሱ ነው ብላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

ሩዋንዳ M 23 የተሰኘውን የኮንጎ ኪንሻሣ አማጺ ቡድን እየረዳች እና እየደገፈች መሆኑ ይነገራል፡፡

 

ከጥቂት ወራት በፊት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮንጎ እና የሩዋንዳ መሪዎችን ወደ ዋይት ሐውስ በማስጠራት የሰላም ስምምነት ቢያስፈርሟቸውም በምስራቃዊ ኮንጎ ኪንሻሣ አሁንም ድረስ ጦርነቱ መቆሚያ አላገኘም፡፡

 

ለዚህም የአሜሪካ መንግስት የሩዋንዳን ጦር በስምምነት ጣሽነት እየከሰሰ ነው፡፡

 

ሩዋንዳ የ M 23 አማጺያንን እየረዳች ነው ቢባልም እሷ ግን በተደጋጋሚ እኔ የለሁበትም ባይ ነች፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

YouTube : https://shorturl.at/18TS1                   

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page