የኒጀር ወታደራዊ መንግስት አሜሪካን በቃ ወታደሮችሽን ከሀገሬ አስወጪልኝ አለ፡፡
የኒጀር ወታደራዊ መንግስት ለአሜሪካ መሰል ጥያቄ ሲያቀርብ ወር ባልሞላ ጊዜ የትናንቱ 2ኛው እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የምዕራብ አፍሪካዊቱ አገር መንግስት ቀደም ሲል የሁለቱን አገሮች የመከላከያ ትብብር ስምምነት አያሻኝም ማለቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በጊዜውም የወታደራዊ መንግስት መሪው የአሜሪካ ወታደሮች ኒጀርን ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በኒጀር ከ600 በላይ ወታደሮች እንዳሏት ይነገራል፡፡
የኒጀር ወታደራዊ መንግስት ቀደምሲል በዚያ የነበሩ የፈረንሳይ ወታደሮችን በሙሉ አስወጥቷል፡፡
የሩሲያ ወታደሮች ከአቭዲቭካ በስተምዕራብ ይዞታቸውን እያስፋፉ ነው ተባለ፡፡
ሩሲያውኑ በዳኔስክ ግዛት የምትገነውን አብዲቭካን የያዟት ከወር ተኩል በፊት እንደሆነ ኒውስ ዊክ አስታውሷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሩሲያ ወታደሮች ከአብዲቭካ በስተምዕራብ ያሉ ስፍራዎችን እየተቆጣጠሩ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የሩሲያ ጦር ከወር ተኩል በፊት አቭዲቭካን እንደተቆጣጠረ በስተምዕራብ አቅጣጫ ለመግፋት በጥሩ የጦር ቁመና ላይ እገኛለሁ ብሎ ነበር፡፡
የዩክሬይን ወታደራዊ ሹሞችም የሩሲያ ጦር አዲስ ጥቃት ሊከፍትብን ነው ብለው እንደነበር በዘገባው ለትውስታ ሰፍሯል፡፡
ስለ አዲሱ የሩሲያ ጦር የተስፋፋ ይዞታ ከዩክሬይን ሹሞች በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡
የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን እና የፈረንሳይ አቻቸው ስቴፋን ሴዢርኒ ለዩክሬይን ያልተቆጠበ ድጋፍ እናደርግላታለን አሉ፡፡
ዩክሬይን ከሩሲያ ጋር ስትዋጋ ከ2 አመታት በላይ ሆኗታል፡፡
ምዕራባዊያን እና አጋሮቻቸው ዩክሬይንን በጦር መሳሪያ እና በወታደራዊ መረጃ እየደገፏት እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
የፈረንሳይ እና የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዩክሬይን የሁለቱ አገሮች ድጋፍ እንደማይቋረጥባት በጋራ መግለጫቸው እወቁልን ብለዋል፡፡
ዩክሬይን በጦርነቱ የግዴታ ማሸነፍ አለባት ብለዋል፡፡
ዩክሬይን በጦርነቱ ከተሸነፈች አገሮቻቸው እንደተሸነፉ እንደሚቆጥሩት እወቁልን ብለዋል፡፡
ሩሲያ በፊናዋ በጦርነቱ እያሸነፍኩ ነው ባይ እንደሆነች በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በቻዷ ርዕሰ ከተማ እንጃሚና የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ ጄኔራል ማኅማት ኢድሪስ ዴቢ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሰሌዳ እየተሰቀለ ነው ተባለ፡፡
የማኅማት ኢድሪስ ዴቢ ሰሌዳ መሰቀል የያዘው የምረጡን ዘመቻው ሊጀመር ከሳምንት በላይ እየቀረው መሆኑን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበራት የወታደራዊ መሪው ምስል እና ፖለቲካዊ መልዕክት ከጊዜው አስቀድሞ መለጠፍ እና መሰቀሉን የህግ ጥሰት ነው ብለውታል፡፡
ዴቢ ከጊዜው የቀደመ ቅስቀሳቸውን እንዲያቆሙ ተቃዋሚዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ቻድ በምርጫ ጥሩ ስም እንደሌላት በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ማሐማት ኢድሪስ ዴቢ በአማጺያን ጥቃት ከ3 አመታት በፊት በተገደሉት አባታቸው ወንበር ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣን እንደጨበጡ ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: @ShegerFMRadio102_1
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments