በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት በኢትዮጵያ በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ተናገረ፡፡
- 1 day ago
- 2 min read
መጋቢት 22/2018
በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት በኢትዮጵያ በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ተናገረ፡፡
የኢራኑ ጦርነት በአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥም እየፈጠረ መሆኑን ኮሚቴው ማስታወሱን ከብሔራዊ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ይህም በሃገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ጠቅሶ የስጋቱ ጫና ግን መንግስት በሚወስደው የመቆጣጠሪያ እርምጃዎች እና ግጭቱ በሚቆይበት ጊዜ የሚወሰን ይሆናል ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊስ ኮሚቴው ስድስተኛ ዙር ስብሰባውን አካሄዶ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በመገምገም መግለጫ አውጥቷል፡፡
በቅርቡ ሁለት ገለልተኛና የመስኩ ባለሙያ የሆኑ አባላትን ያካተተው የገንዘብ ፖሊሲ ከታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት ተመዝግቦ መቆየቱን ተናግሯል፡፡
በዘላቂነት ለማስቀጠልም እየተወሰደ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ሊቀጥል ይገባል ሲል ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል፡፡
ለዚህም ብሔራዊ ባንክ ያሉትን የፖሊሲ አላማዎች ሁሉ በሙሉ እንዲጠቀም አሳስቧል፡፡
ቀደም ሲልም ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው እንዲቀጥል በመወሰኑ ምክንያት በባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየው የብድር ገደብ ተሻሽሎ መቀጠሉ ይታወሳል፡፡

አሁንም ባለበት ይቀጥል የሚል ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በሌላ በኩል ብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ገበያውን ለማረጋጋት በሚል በሚያወጣቸው ጨረታዎች በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከገበያው እየሰበሰበ መሆኑም አንዱ የጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲው የገንዘብ ሁኔታን በተመለከተ በመግለጫው ባካተተው ሀሳብ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦት ከአምናው በ39.3 በመቶ ማደጉን ጠቅሷል፡፡
በባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየው የብድር ገደብ ተሻሽሎ ሲቀጥል በተወሰነ መልኩ የብድር አቅርቦት ለመጨመሩ ለገንዘብ አቅርቦት እድገቱ ምክንያት ሆኗልም ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል መሰረታዊ የገንዘብ እድገት መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ በኢኮኖሚው የሚዘዋወረውን የገንዘብ ስርጭት እየሰበሰበ መሆኑ ለመሰረታዊ የገንዘብ እድገት መቀነስ ምክንያት ሆኗል፡፡
ባንኩ 500 ሚሊዮን ዶላር ለጨረታ ባቀረበበት አንድ የጨረታ ጊዜ ያቀረበውን ዶላር ሙሉ ቢሸጥ ብቻ ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ የሚያስችል መሆኑ ይታወቃል፡፡
በገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ግምገማ መሰረት የበጀት ጉድለት ሁኔታው ከአጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት አንፃር ከአምናው በዜሮ ነጥብ ሰባት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ምንም እንኳን የገቢ አሰባሰቡ በ2018፣ 7 ወራት በ65 በመቶ እድገት ቢያሳይም አጠቃላይ ሃገራዊ ወጭው 48 በመቶ በመጨመሩ የበጀት ጉድለቱ እንዲሰፋ አድርጓል ብሏል ኮሚቴው፡፡
መንግስታዊ ወጭ በምን ሰበብ በ48 በመቶ እንደጨመረ ግን በመግለጫው አላብራራም፡፡
ያም ሆኖ የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት ብሔራዊ ባንክ አንድም ብር ለመንግስት አላበደረም ፣ የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድን ለገበያ በማቅረብ ግን በሰባት ወራት 136.6 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል ብሏል፡፡
ከግምጃ ቤት ሰነድ የተገኘው ገንዘብ የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷልም ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ምክረ ሀሳብ ከሰጠባቸው ጉዳቶች መካከል በባንኮች ተጥሎ የቆየው የብድር ገደብ አንዱ ነው፡፡
የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ሲባል ገደቡ በነበረበት እንዲቀጥል ወስኗል፡፡
ነገር ግን በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ የሚታየው ተለዋዋጭ የአለም የኢኮኖሚ ሁኔታ በኢትዮጵያም ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ከግንዛቤ በማስገባት በንቃት መገምገም ያስፈልጋል ሲል አሳስቧል፡፡
ይህንኑ በተመለከተም ኮሚቴው ተጨማሪ የፖሊሲ እርምጃዎች ያስፈልጉ እንደሆነ ለመገምገም በመጭው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ወይም እንዳስፈላጊነቱ ቀደም ብሎ እንዲሰበሰብ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7




Comments