የታይዋኗ ርዕሠ ከተማ ታይፔ የቀድሞ ከንቲባ በጉቦ ቅሌት የ17 አመታት የእስር ቅጣት ተከናነቡ፡፡
- Mar 27
- 3 min read
መጋቢት 18/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
የታይዋኗ ርዕሠ ከተማ ታይፔ የቀድሞ ከንቲባ በጉቦ ቅሌት የ17 አመታት የእስር ቅጣት ተከናነቡ፡፡
ኮ ዌን ጄ የተባሉት የታይፔ የቀድሞ ከንቲባ ለ17 አመታት እስር ቅጣት የተዳረጉት የ532 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የምንዛሪ ግምት ያለው ገንዘብ በጉቦ መቀበላቸው ተረጋግጦባቸው እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡

በተሰጣቸው ጉቦ ለውጥ ለሪል ስቴት አልሚዎች ከተፈቀደላቸው በላይ ሰፊ መሬት መምራታቸው ታውቋል፡፡
ግለሰቡ በጠበቆቻቸው አማካይነት ይግባኝ መጠየቃቸው ተጠቅሷል፡፡
ጉዳያቸው በይግባኝ እስኪታይም በዋስ ሆነው ውጤቱን ይጠባበቃሉ ተብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በሰላሙ ጉዳይ ያለ አንዳች ማንገራገር ካልተስማማች ከእስካሁኑም የከፋ ከባድ ድብደባ ይጠብቃታል ሲሉ ዛቱባት፡፡
ትራምፕ ቀደም ሲል ከኢራን ሹሞች ጋር ገንቢ ንግግር እያከናወኑ መሆኑን ሲናገሩ መሰንበታቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
የኢራን ሹሞችም ከአሜሪካ ጋር አንዳችም ንግግር አላደረግንም ፤ ማድረግም አንፈልግም እያሉ ነው፡፡
አሜሪካ ለጦርነቱ ማብቃት የተሰናዳ ነው የተባለ ባለ 15 ነጥቦች እቅድ በፓኪስታን በኩል ለኢራን መላኳ እየተነገረ ነው፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አገራቸው በአሜሪካ ባለ 15 ነጥቦች እቅድ በጭራሽ እንደማትስማማ ቀደም ሲል ተናግረዋል፡፡
እንደሚባለው የአሜሪካ ባለ 15 ነጥቦች እቅድ ኢራን የኒኩሊር ተቋማቷን ሁሉ ከጥቅም ውጭ እንድታደርግ ይጠይቃል፡፡
ከእንግዲህም በማንኛውም ደረጃ ዩራኒየም የተሰኘውን ንጥረ ነገር እንዳታብላላ ይከለክላታል፡፡
በእጅጉ የተብላላ ዩራኒየም የኒኩሊር የጦር መሳሪያ ዋነኛ ግብአት ነው ይባላል፡፡
አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል በ3 የባህረ ሰላጤው አገሮች የአሜሪካ የጦር ድርጅቶች መገኛዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን አድርሻለሁ አለ፡፡
የኢራኑ የጦር ክፍል ጥቃቶቹን ሰንዝሬያለሁ ያለው በኩዌት ፣ በሳውዲ አረቢያ እና በባሕሬን በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ተቋማት እና ድርጅቶች ላይ ነው ማለቱን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
በኩዌት አሪፍጃን ፣ በሳውዲ አረቢያ አልካርጅ እና በባሕሬን ሼክ ኢሣ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን መትቻለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
አብዮታዊ ዘቡ በባህረ ሰላጤው የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ያደረስኩት በደቡባዊ ምዕራብ ክፍላችን ለተፈፀመብን ድብደባ አፀፋ ነው ብሏል፡፡
በአፀፋችን ከተመቱት ውስጥ የአሜሪካ የስንቅ እና ትጥቅ ማዕከሎች ፣ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች እና የሰው አልባ በራሪ አካላት /ድሮኖች/ መጠለያዎች ይገኙበታል ማለቱ ተጠቅሷል፡፡
ድብደባው የተሳካ እንደነበር የጦሩ ሹሞች ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የኤሌክትሪክ አውታሮች ለመምታት አለኝ ያሉትን እቅድ ስራ ላይ ማዋያውን ጊዜ በተጨማሪ 10 ቀናት አራዝሜለሁ አሉ፡፡
ትራምፕ በቅድሚያ ለኢራን የ48 ሰዓት ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር፡፡
ከዚያም ለተጨማሪ 5 ቀናት አራዝመውት እንደነበር አልጀዚራ አስታውሷል፡፡
ትራምፕ አሁን ደግሞ የኢራንን የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች በሙሉ ለማውደም የነበራቸውን እቅድ በተጨማሪ 10 ቀናት ማራዘማቸው ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት የጊዜ ገደብ ማራዘሚያ አድርጌያለሁ ያሉት ከኢራን ጋር የሚካሄደውን ንግግር መልካም እርምጃ እየታየበት መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡
የኢራን ሹሞች ግን አንዱ ከሌላው እየተከታተሉ ከአሜሪካ ጋር የተደረገ አንዳችም ንግግር የለም በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡
ትራምፕ ከኢራን ሹሞች ጋር እየተነጋገርን ነው ማለታቸው አሁንም በውዥንብር እንደተሞላ ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት የኢራንን የኤሌክትሪክ አውታሮች ለማውደም የዛቱት አገሪቱ ዘግታዋለች የተባለውን የሆርሙዝን የባህር መተላለፊያ ሰርጥ ያለ አንዳች እክል መሰናክል እንድትከፍት ለማስገደድ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡
የየመን ሁቲዎች ንቅናቄ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በኢራኑ ጦርነት በቴሕራን ደጋፊነት እገባበታለሁ ማለቱ ተሰማ፡፡
የንቅናቄው መሪ አብዱልማሌክ አል ሁቲ በኢራኑ ጦርነት ጉዳይ ገለልተኞች አይደለንም ሲሉ መናገራቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
የሁቲዎቹ መሪ ኢራንን በጦር እንደሚያግዙ ሲናገሩ የትናንቱ የመጀመሪያው አይደለም ተብሏል፡፡
ሆኖም ሁቲዎቹ ከንግግር ያለፈ ለኢራን በአሁኑ ጦርነት ያደረጉት አንዳችም የጦር ድጋፍ እንደሌለ ተጠቅሷል፡፡
በእስራኤል የጋዛ ዘመቻ ወቅት ሁቲዎቹ በእስራኤል ላይ የሚሳየል እና የድሮን ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል፡፡
በቀይ ባህርም የእስራኤል ወዳጆች ናቸው ያሏቸው መርከቦች እንዳይተላለፉ ዒላማቸው አድርገዋቸው ነበር፡፡
ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የፖለቲካ እና የጦር አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments