ግንቦት 20 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- 2 days ago
- 2 min read
በጋዛ ሰርጥ የምግብ እርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል ከፍተኛ ረብሻ እና ውጥንቅጥ ተፈጠረ፡፡
ለ3 ወራት ምናምኒት ሰብአዊ እርዳታ ያላገኙ ፍልስጤማውያን ወደ እርዳታ ማከፋፈያው መጉረፋቸው ቀድሞ ለመግባት በተፈጠረ መተፋፈግ ረብሻው መፈጠሩን አልጀዚራ ፅፏል፡፡

ረብሻ የተፈጠረበት የጋዛ የእርዳታ ማከፋፈያ በአሜሪካ እና በእስራኤል የእርዳታ አቅራቢዎች የሚመራ ነው ተብሏል፡፡
የተፈጠረው ግርግር እና ሁከት ከቁጥጥር ውጭ እንደነበር ተሰምቷል፡፡
እርዳታ ፈላጊዎቹንም ለመበተን ወታደሮች ተኩስ ከፍተው ነበር ተብሏል፡፡
እስራኤል ለ3 ወራት ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባ ማድረጓ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳ እና ተቃውሞ አበርትቶባት ሰንብቷል፡፡
ቀደም ሲል እስራኤል በጋዛ በቂ የምግብ ክምችት አለ የሚል መሟገቻ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡
በሱዳን የኮሌራ ወረርሽኝ የሚገድላቸው ሰዎች ብዛት እየጨመረ ነው ተባለ፡፡
ወረርሽኙ በ1 ሳምንት ጊዜ 172 ሰዎችን መግደሉን የጤና ሹሞች እንደተናገሩ አናዶሉ ፅፏል፡፡
አብዛኞቹ ሰዎች በኮሌራ የሞቱት በካርቱም ግዛት መሆኑ ታውቋል፡፡
በካርቱም ግዛት የተለያዩ ክፍሎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ነበር፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ውጊያ ከገጠሙ ከ2 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት መውደማቸው ይነገራል፡፡
በዚያ ላይ ኤሌክትሪክ እና ንጹህ ውሃ ማግኘቱ በእጅጉ አዳጋች እየሆነ መምጣቱ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
የብሪታንያው ንጉስ ቻርልስ ካናዳ ከአሁን በላይም ይበልጥ ጠንካራ ትሆናለች አሉ፡፡
ንጉሱ በካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ ግብዣ ለአገሪቱ ፓርላማ ንግግር ማድረጋቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ንጉስ ቻርልስ የካናዳም ርዕሰ ብሔር ናቸው፡፡
የንጉሱ የካናዳ ፓርላማ ንግግር ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ካናዳ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት መሆኗ አይቀርም ሲሉ መናገራቸውን የተከተለ ነው፡፡
የብሪታንያው ንጉስ ካናዳ ጠንካራም ነፃም ሆና ትዘልቃለች ሲሉ ለአገሪቱ ፓርላማ ተናግረዋል፡፡
ንጉሱን በካናዳ ታላቅ እና ደማቅ አቀባበል ጠብቋቸዋል፡፡
የካናዳ የፖለቲካ መሪዎች ንጉሱ አገሪቱን እንዲጎበኙ መጋበዛቸው ለትራምፕ ውጥን ምላሽ ተደርጎ መተርጎሙን መረጃው አስታውሷል፡፡
በቻይና ሻን ዶንግ በአንድ የኬሚካል ማምረቻ ኢንዱስትሪ የደረሰ ከባድ ፍንዳታ በጥቂቱ 5 ሰዎችን ገደለ፡፡
በፍንዳታው ሕይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ 19 ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በኢንዱስትሪው ላይ የደረሰው ፍንዳታ በእጅጉ ከባድ ነበር ተብሏል፡፡
በአደጋው ሕይወታቸው ካለፈው እና አካላዊ ጉዳት ከገጠማቸው በተጨማሪ 6 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት እንዳልታወቀ ተጠቅሷል፡፡
ፍንዳታው የአቅራቢያውን ሕንፃዎች መስኮቶች ጭምር መሰባበሩ ታውቋል፡፡
በኢንዱስትሪው ፍንዳታው በምን ምክንያት እንደተከሰተ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም፡፡
ከ6 ዓመት በፊትም ያንቼንግ በተባለ ስፍራ በሚገኘ ሌላ የኬሚካል ኢንዱስትሪ አጋጥሞ በነበረ ፍንዳታ የ78 ሰዎች ሕይወት ማለፉን መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
Comments