top of page

ግንቦት 12 2017  -  የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • May 20
  • 2 min read

 

ፈረንሳይ በደቡብ አሜሪካ አማዞን ጫካ ውስጥ ከፍተኛ ጥበቃ የማይለየው እስር ቤት ልትገነባ ነው ተባለ፡፡

 

የፈረንሳዩ የፍትህ ሚኒስትር ጌራልድ ድራማኒን ፍሬንች ጉያና በተባለው የፈረንሳይ የባህር ማዶ ግዛት እስር ቤቱ እንደሚገነባ መናገራቸውን ዘ ቴሌግራፍ ፅፏል፡፡

 

የፍትህ ሚኒስትሩ እስር ቤቱ በዚያ እንዲገነባ ወስኛለሁ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

እስር ቤቱ የአደገኛ ዕፅ አስተላላፊዎች ፣ የአሸባሪዎች እንዲሁም የከባድ ወንጀለኞች መታሰሪያ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

 

በፈረንሳይ ጉያና የሚቋቋመው እስር ቤት አደገኛ ወንጀለኞችን ነጥሎ መቅጣት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡

 

ጉያናም ራሷ ከባድ ወንጀል የሚበዛበት ግዛት ነች ተብሏል፡፡

 

ፈረንሳይ ያቀደችው ከፍተኛ ጥበቃ የማይለየው የጉያና እስር ቤት ከ2 አመት ተኩል በኋላ ስራ እንደሚጀምር በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

 

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ እና ዩክሬይን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ንግግር ይጀምራሉ አሉ፡፡

 

ትራምፕ ሁለቱ ተፋላሚ አገሮች የተኩስ አቁም ንግግር ይጀምራሉ ያሉት ከሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ትናንት ከ2 ሰዓት በላይ የጠየቀ የስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡

 

የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን በደፈናው ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችለውን መንገድ ይዘናል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

በሁለቱ አገሮች መካከል ቀጥተኛ ንግግር እንዲደረግ ለተወጡት ድርሻ ፑቲን ትራምፕን አመስግነዋል ተብሏል፡፡

 

ትራምፕ አጣዳፊ የተኩስ አቁም መደረግ አለበት ሲሉ ፑቲን በበኩላቸው ከዩክሬይን ጋር ተገቢው ስምምነት ከተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚያደርጉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

 

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ከሩሲያው አቻቸው በተጨማሪ ከዩክሬይኑ ፐከአውሮፓ ኃያላን መሪዎች በዚሁ ጉዳይ በስልክ መነጋገራቸው ታውቋል፡፡

 

የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለአጣዳፊው የተኩስ አቁም በሩሲያ ላይ በተጨማሪ ማዕቀብ የታገዘ ግፊት ሊደረግባት ይገባል ማለታቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

 

 

የሱዳን ወታደራዊ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ነባሩን ዲፕሎማት ካሚል ኢድሪስን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሾሟቸው፡፡

 

ኢድሪስ በጠቅላይ ሚኒስትር የተሾሙት በአገሪቱ የሚካሄደው ጦርነት ከ2 አመታት በላይ ባስቆጠረበት አጋጣሚ እንደሆነ አሽራቅ አል አውሳት ፅፏል፡፡

 

ካሚል ኢድሪስ ከወር በፊት በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሰይመው የነበሩትን ዳፋላ አል ሐጅን ተክተዋቸዋል ተብሏል፡፡

 

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቀደመው ጊዜ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል ተብሏል፡፡

 

የሱዳኑ ወታደራዊ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ቀደም ሲል የጦር ወቅት የባለሙያዎች አስተዳደር ስራ ላይ እንደሚያውለው ተናግረው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

ብሪታንያ እና ኢራን አንዷ የሌላኛዋን አገር ዲፕሎማሲያዊ ወኪሎች ለማብራሪያ አስጠሩ ተባለ፡፡

 

ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ወኪሎችን ያስጠሩት ብሪታንያ ሰላዮች ናቸው ያለቻቸውን ሶስት ኢራናውያን ማሰሯን ተከትሎ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

ከሁለት ሳምንታት በፊት የተያዙት 3 ኢራናውያን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለንደን ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል፡፡

 

ኢራናውያኑ ለአገራቸው በመሰለል ክስ እንደተመሰረተበቸው ተጠቅሷል፡፡

 

እንደሚባለው ኢራናውያኑ ቀደም ሲል ጥገኝነት ጠይቀው ጊዜያዊ ፈቃድ ያገኙ ናቸው፡፡

 

የብሪታንያ ሹሞች ግለሰቦቹን በሰላይነት ያሰማሯቸው የኢራን ባለስልጣናት ናቸው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ኢራን ከምዕራባዊያን ኃያላን ጋር ያላት ግንኙነት በእጅጉ የደፈረሰ መሆኑ ይነገራል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

 

📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN

Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page