top of page

ግንቦት 11 2017 የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • May 19
  • 2 min read

የሱዳን መንግስት ጦር በዳርፉር ግዛት አትሩን የተባለውን አካባቢ ከRSF ታጣቂዎች ቀምቼ ተቆጣጥሬአለሁ አለ፡፡


አትሩን ወታደራዊ ፋይዳው የጎላ ስፍራ ነው መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ይሄን አካባቢ ከRSF ለመቀማት በተካሄደው ውጊያ የሱዳን መንግስት ጦር ተባባሪዎችም አብረው ተሰልፈው ነበር ተብሏል፡፡

ree

በውጊያው RSF በሰው ሀይልም ሆነ በቁሳቁስ ከፍተኛ ኪሳራ እንደገጠመው የሱዳን መንግስት የጦር ሹሞች ተናግረዋል፡፡


RSF የአትሩንን አካባቢ የተቆጣጠረው ከወር በፊት በተካሄደ ውጊያ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የአትሩንን አካባቢ መልሶ ተቀምቷል ስለመባሉ ማረጋገጫም ይሁን ማስተባበያ አልሰጠም፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF በመካከላቸው ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ ከ2 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡



የሜክሲኮ ባህር ሀይል የመለማመጃ መርከብ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከብሩክሊን ድልድይ ጋር በመጋጨቱ ሁለት ሰዎች መሞታቸው ተሰማ፡፡


በአደጋው ሕይወታቸው ካለፈው ሌላ 19ኙ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደገጠማቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡


አካላዊ ጉዳት የገጠማቸው ለሕይወታቸው ያሰጋቸዋል ተብሏል፡፡


የመለማመጃ መርከቡ 277 ሰልጣኝ የባህር ሀይል ባልደረቦችን አሳፍሮ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡


መርከቡ በሜካኒካዊ እክል የተነሳ የኤሌክትሪክ መጥፋት የገጠመው መሆኑ ከድልድዩ ምሰሶ ጋር እንዲላተም ምክንያት እንደሆነ ተገምቷል፡፡


በአደጋው ድልድዩ አንዳችም ጉዳት አልደረሰበትም ተብሏል፡፡


የሜክሲኮዋ ፕሬዘዳንት ክላውዲያ ሺንባውም በአደጋው ከልብ አዝኛለሁ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



የኬንያዋ የቀድሞ የፍትህ ሚኒስትር ማርታ ካሩአ ከታንዛኒያ ተገድደው እንዲወጡ ተደረገ፡፡


ካሩአ በታንዛኒያ የተገኙት የተቃዋሚውን ቻዴማ የፖለቲካ ማህበር መሪ ቱንዱ ሊሱን የፍርድ ሒደት ለመከታተል ነበር ተብሏል፡፡


ሴትዮዋ ከወር በፊትም ይሄንኑ ጉዳይ ለመከታተል በታንዛኒያ ፍርድ ቤት ተገኝተው እንደነበር የኬኒያው ካፒታል ኒውስ አስታውሷል፡፡


የኬኒያ ሹሞች የታንዛኒያ መንግስት ካሩአን ያባረረበትን ምክንያት አልጠቀሰልንም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ከካሩዋ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት የኬኒያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም አብረው ከታንዛኒያ ተገድደው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡


ካሩአ ራሳቸው ከፖለቲከኝነታቸው በተጨማሪ በሰብአዊ መብት ተከራካሪነታቸው እንደሚታወቁ መረጃው አስታውሷል፡፡



የየመኑ ሰንዓ አለም አቀፍ ኤርፖርት ከ10 ቀናት መቋረጥ በኋላ ወደ ሙሉ አገልግሎቱ ተመለሰ ተባለ፡፡


ቀደም ሲል የየመን ሁቲዎች ኤርፖርቱ በእስራኤል ከባድ የአየር ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር መናገራቸውን አናደሉ አስታውሷል፡፡


እስራኤል በኤርፖርቱ ላይ ድብደባ የፈፀመችው ሁቲዎቹ ወደ እስራኤል ቤንጉሪዮን ኤርፖርት ባልስቲክ ሚሳየል ከተኮሱ በኋላ ነበር፡፡


ሁቲዎቹ በእስራኤል ላይ የሚሳየል እና የድሮን ጥቃት የሚሰነዝሩት ለጋዛ ፍልስጤማውያን አጋርነታቸው ለማሳየት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡


እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ማካሄድ ከጀመረች አንስቶ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ብዛት ከ53 ሺህ መብለጡ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


የየመኗን ርዕሰ ከተማ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page