የፔሩ ፓርላማ ጆሴ ማሪያ ባልካዛርን የሀገሪቱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰየመ።
- 18 minutes ago
- 3 min read
የካቲት 13/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
የፔሩ ፓርላማ ጆሴ ማሪያ ባልካዛርን የሀገሪቱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰየመ።
ፓርላማው ቀደም ብሎ ለአራት ወራት በተጠባባቂ ፕሬዝዳነትነት ያገለገሉትን ጆሴ ጄሪ በሙስና ምክንያት ከስልጣን ማንሳቱ ይታወሳል።

አሁን የተመረጡት ፕሬዝዳንት ጆሴ ማሪያ ባልካዛር የፓርላማው አባል እንደሆኑ ተነግሯል
በአስር ዓመት ውስጥ በፔሩ ስምንት ፕሬዝዳንቶች መፈራረቃቸውን ሮይተርስ ጽፏል።
ሀገሪቱ ሚያዝያ ወር ላይ ፕሬዝደንቷን እና የፓርላማ አባላትን ምርጫ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዛለች።
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር በዲኤጎ ጋርሺያ የአየር ሃይል ሰፈር ዙሪያ የደረሱት ስምምነት ትልቅ ስህተት ያለበት ነው ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቹ።
ዲኤጎ ጋርሺያ በህንድ ውቅያኖስ ላይ በምትገኘው እና የደሴቶች ስብስብ በሆነችው ቻጎስ ውስጥ ያለ የአየር ሃይል ሰፈር ነው።
የአየር ሃይል ሰፈሩን ብሪታንያና አሜሪካ በጋራ እንደሚገለገሉበት ታይምስ ላይቭ ጽፏል።
ባለፈው አመት የደሴቶች ስብስብ የሆነችው ቻጎስ የሞሪሺየስ ሉአላዊ አካል መሆኗን በመቀበል ብሪታንያ ስምምነት ፈርማለች።
የአየር ሃይሉን ግን ለ99 ዓመታት በሚቆይ የሊዝ ውል እያስተዳደረችው ልትቆይ ነው የተስማማችው ።
በሀገር ደረጃ የሊዝ ውል የሚመከር አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር እንዲህ አይነት ስምምነት በመድረሳቸው ትልቅ ስህተት መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡
የአየር ሃይል ሰፈሩ ወደፊት በኢራን ላይ ሊወሰድ ለሚችል እርምጃ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አንድ ሺህ የሚሆኑ የኬንያ ዜጎች ከሩስያ ጎን ተሰልፈው ዩክሬንን ለመውጋት መመዝገባቸው ተነገረ።
መረጃውን ይፋ ያደረገው የኬንያ የስለላ መስሪያ ቤት እንደሆነ ቢቢሲ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ጽፏል።
ሰማንያ ዘጠኝ ኬንያውንም ደግሞ አሁን ላይ ከሩስያ ጎን ተሰልፈው ዩክሬንን እየወጉ እንደሚገኙ መረጃው አመልክቷል።
የስለላ መስሪያ ቤቱ መረጃውን ለሀገሪቱ ፓርላማ መላኩ ተነግሯል።
ኬንያ ከሠሞኑ ዜጎቿ ለሌሎች ሀገራት በቅጥረኝነት ከመዋጋት እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ መስጠቷ ይታወሳል።
ናይጄያም እንዲሁ ዜጎቿ ለሌሎች ሀገራት በቅጥረኝነት ከመዋጋት እንዲቆጠቡ አሳስባለች።
ከሩስያ ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩ ሁለት ናይጄሪያውያንን አስከሬን እንዳገኘች ዩክሬን ከቀናት በፊት ይፋ አድርጋለች።
ናይጄሪያውያኑ ከሩስያ ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የተገደሉት በምስራቃዊ ዩክሬን ሉዋንስክ እንደሆነ ኬቭ ጠቅሳለች።
የተገደሉትም በሰው አልባ በራሪ አካል ወይም ድሮን ጥቃት ነው ብላለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትኒያሁ ሳይጠበቅ የጸጥታ ካቢኔያቸው ስብሰባ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ማድረጋቸው ተሰማ።
ውሳኔው አሜሪካ በቀናት ውስጥ በኢራን ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች የሚለውን ግምት ከፍ እንዳደረገው የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
አሜሪካ እና ኢራን ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ እያደረጉት ያለው ድርድር ብዙም ውጤት እያመጣ አይደለም ተብሏል።
ኢራን የአሜሪካንን ጥያቄዎች ለመቀበል ፍቃደኛ እንዳልሆነች ነው የተነገረው።
ይህን ተከትሎም አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚለው ግምት እያደገ መጥቷል።
የአሜሪካ ጦርም ለእርምጃው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ትዕዛዝ ብቻ እየጠበቀ እንደሚገኝ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ልጅ ቤላርማይን ሙጋቤ ሰው ለመግደል በመሞከር ወንጀል ተጠርጥሮ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የ28 ዓመቱ ቤላርማይን ሙጋቤ አንድን የ23 ዓመት ወጣት ጆሃንስበርግ ውስጥ ተኩሶ ማቁሰሉ ተነግሯል።
በወንጀሉ ተባባሪው ነበር የተባለ ሌላ ግለሰብም አብሮት በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል።
ሁለቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል።
ቤላርማይን ሙጋቤ ሟቹ የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሁለተኛ ባለቤታቸው ከነበሩት ግራሻ የወለዱት በዕድሜ ትንሹ ልጃቸው እንደሆነ መረጃው ጠቅሷል።
የተተኮሰበት ወጣት በሆስፒታል የሚገኝ ሲሆን የደረሰበት ጉዳት ለህይወቱ ያሰገዋል ተብሏል።
ለ37 ዓመታት ዚምባብዌን የመሩት ሮበርት ሙጋቤ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በህዝባዊ ተቃውሞ ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።
ስልጣን ከለቀቁ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት ( ሃማስ) አዲስ ጊዜያዊ መሪ ለመሰየም ምርጫ እያካሄደ እንደሚገኝ ተነገረ።
የቡድኑ አብዛኞቹ ከፍተኛ አመራሮች በእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።
በጋዛ ሰርጥ ፤ በዌስት ባንክ እና ሌሎች አካባቢዎች ያሉ የሃማስ አባላት አዲሱን መሪ ለመሰየም ድምጽ እየሰጡ ይገኛሉ ተብሏል።
የሚመረጠው ጊዜያዊ መሪ የአንድ ዓመት የስልጣን ቆይታ እንደሚኖረው የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በጋዛ የሃማስ መሪ የሆኑት ካሊል አል ሃያ እና በውጪ አገር የሃማስ ክንፍ መሪ ካሊድ መሻል በምርጫው ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ተገምቷል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7












Comments