top of page

በቁም እንስሳት ሃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗ በሚነገርላት ኢትዮጵያ፤ የስጋ ምርት ለምን እንዲህ ተወደደ?

  • 3 hours ago
  • 2 min read

ሚያዝያ 8/2018


በቁም እንሰሳት ሃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗ የሚነገርላት ኢትዮጵያ የስጋ ምርት እንደልብ የማይገኝባት፣ ቢገኝም እንኳን የዋጋው ነገር ለብዙዎች የማይቀመስ በመሆኑ ’’ስጋ’’ የመግዛት አቅም ያላቸው ብቻ የሚያገኙት መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡


በተለይ ልኳንዳ ነጋዴዎች የስጋ ምርት ላይ በሚጣለው አግባብ ያልሆነና ተደራራቢ ግብር ምክንያት ስጋ እንዲወደድ፣ ነጋዴውም ጫና ውስጥ እንዲገባ ሆኗል ይላሉ፡፡


የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ሳህሌ የስጋን ግብር በተመለከተ ከዛሬ 10 ዓመት ጀምሮ ቅሬታችንን ስናቀርብ ቆይተናል ይሁንና እስካሁን ይህ ነው የሚባል ምላሽ አልተሰጠንም ብለውናል፡፡


የገቢ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት የልኳንዳ ቤቶችን ግብር የሚያሰላው በሬው የሚመዝነውን ኪሎ በመውሰድ 1 ኪሎ ስጋ ከሚሸጥበት ዋጋ ጋር በማባዛት ነው የሚሉት አቶ አየለ ይህ በጣም ስህተት ነው፤ በሬው 100 ኪሎ የሚመዝን ቢሆን ሲታረድ የሚወገደው ወደ 40 ኪሎው ነው በጊዚህ መንገድ ግብርን ማስላት ተገቢ እንዳልሆነ ያነሳሉ፡፡


የስጋ ምርት ለሰዎች መሰረታዊ ነው፣ ቢቻል ከግብር ነፃ መደረግ ነበረበት፣ ቢሆን እንኳን የሚጣለው ግብር ከ2 በመቶ መብለጥ አልነበረበትም፣ ለዓመታት ስንወተውት ብንቆይም ሰሚ አጥተን ስጋ በተደራራቢ ግብር ማነቆ ውስጥ ገብቶ በተለይ ደሞዝተኛው ስጋ ብርቅ እየሆነበት ነው ብለዋል የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዝዳንቱ አቶ አየለ ሳህሌ፡፡


በሌላ በኩል ከቀናት በፊት በተከበረው የፋሲካ በዓል ስጋ 650 ብር እንዲሸጥ በንግድ ቢሮ በኩል መወሰኑ ሲታይ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ተገቢ ይመስላል ነገር ግን ይህ ውሳኔ ሲወሰን እነዚህ 650 ብር ሽጡ የተባሉ ነጋዴዎች ከግብር ነፃ አልተደረጉም፤ እንሰሳቱንም የሚገዙት ሌሎች ነጋዴዎች ከሚገዙበት ከተመሳሳይ ገበያ በመሆኑ ልክ ያልሆነ ውሳኔ ሲሉም የማህበሩ ፕሬዚዳንት ተችተዋል፡፡


እነዚህን ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ይዘን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮን ምላሽ ጠይቀናል፡፡



ከዚህ ቀደም ከሰጠነው የተለየ መልስ የለንም ያሉን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ፤ የልኳንዳ ነጋዴዎች ደጋግሞመው የሚሉት ደረሰኝ መቁረጥ አንችልም፤ በቁርጥ ግብር እንስተናገድ የሚል ነው፤ እኛ ደግሞ በአዋጁ መሰረት ነው የምንሰራው፤ አዋጁ በደረሰኝ እንዲከፍሉ ነው የሚያዘው እኛም እያደረግን ያለነው ይህንኑ ነው ብለውናል፡፡


በተጨማሪም ግብሩ ሲሰላ በእርድ ወቅት ውጋጅ ተብሎ የሚጣለው ታሳቢ ይደረግልን የሚሉትን ነገር አንቀበልም ያሉን አቶ ሰውነት፤ እኛ ባለን መረጃ አብዛኛው ልኳንዳ ቤት ከቄራ ይልቅ በራሱ የሚያሳርደው ይበልጣል፤ ይህ ደረሰኝ ላለመቁረጥ የሚደረድሩት ሰበብ ነው፤ የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡


የልኳንዳ ነጋዴዎቹ እንሰሳቱን ሲገዙ ከገበሬ በመሆኑ ደረሰኝ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ደጋግመው ነግረውናል የሚለው ቢሮው እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የእህል ነጋዴዎችም የሚገጥማቸው ችግር ተመሳሳይ በመሆኑ ታሳቢ የሚደረግበት አሰራር እንዳለም ከአቶ ሰውነት ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page