top of page

የኢራን ሹሞች አሜሪካን በሚሳየሎቻችን አትምጪብን አሏት፡፡

  • 9 hours ago
  • 2 min read


የኢራን ሹሞች አሜሪካን በሚሳየሎቻችን አትምጪብን አሏት፡፡


የኢራን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኢስማየል ባጋይ የኢራን የሚሳየል መርሐ ግብር አሜሪካ እና ኢራን በደረሱት የጦርነት ማቆሚያ የመግባቢያ ስምምነት አንድም ስፍራ አልተጠቀሰም ማለታቸውን ሬውተርስ ፅፏል፡፡


ቃል አቀባዩ ሚሳየላችን ለተኩስ እንጂ ለድርድር አይቀርብም ሲሉ መሳለቃቸውም ተሰምቷል፡፡


ከአሜሪካ ሹሞች በኩል የኢራን የሚሳየል መርሐ ግብር የወደፊቱ ድርድር አካል ነው የሚለው አስተያየት እየተደጋገመ ነው ተብሏል፡፡


የኢራን ሹሞች ደግሞ ምንም ቢፈጠር ሚሳየሎቻችን ለድርድር አይቀርቡም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡

በመግባቢያ ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች ኢራን እና አሜሪካ በ60 ቀናት ውስጥ ድርድር እንደሚያደርጉ በሰነዱ ላይ መስፈሩን መረጃው አስታውሷል፡፡



የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ የባህር መተላለፊያ ወሽመጥ የባህር ከበባውን አነሳው፡፡


ጦሩ የሆርሙዝ የባህር ከበባውን ያነሳው አሜሪካ እና ኢራን ለጦርነቱ ማስቆሚያ በደረሱት የመግባቢያ ስምምነት መሰረት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ የባህር ከበባዬን የተውኩት በፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ መሰረት እንደሆነ እወቁልኝ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ሐሚኒ አሜሪካ ወደ ስምምነት ያዘነበለችው ትራምፕ በጦርነቱ የፈለገውን ማሳካት ባለመቻሉ ባደረበት ተስፋ ቆራጭነት ነው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡


የስምምነት ሰነዱ ዛሬ በስዊዘርላንድ በሚከናወን ሥነ ሥርዓት እንደሚፈረም ቀጠሮ የተያዘለት ቀደም ብሎ ነው፡፡


የአደራዳሪዋ አገር ፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ለፊርማው ወደ ስዊዘርላንድ አያመሩም ተብሏል፡፡


ቀደም ብሎ ግን የአሜሪካ እና የኢራን ፕሬዘዳንቶች ዶናልድ ትራምፕ እና ማሱድ ፔዜሽኪያን ሰነዱን ከያሉበት ሆነው በኤሌክትሮኒካዊ መላ መፈረማቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡



የሊባኖስ መንግስት ሔዝቦላህን ትጥቅ ለማስፈታት የሶሪያ ጦር ወደ ሊባኖስ ይግባ መባሉን አጥብቆ ተቃወመው፡፡


የሶሪያ ጦር ወደ ሊባኖስ ዘልቆ ሔዝቦላህን ትጥቅ ያስፈታልን የሚል ሀሳብ ያቀረቡት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡


የሊባኖሱ የፍትህ ሚኒስትር አዴል ናስር ግን ይሄ በጭራሽ የማይሆን ነገር ነው ሲሉ ለCNN መናገራቸውን አናዶሉ ጽፏል፡፡


አዴል ሔዝቦላህን ትጥቅ የማስፈታቱ ጉዳይ የሊባኖስ ሀይሎች ሀላፊነት እንጂ የሌሎች አይደለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ትራምፕ የሶሪያ ጦር ሔዝቦላህን ትጥቅ ያስፈታው ያሉት እስራኤል የሊባኖሱን ጦርነት አቁማ ጦሯን እንድታስወጣ አልመው ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡


አሜሪካ ከኢራን ጋር የደረሰችው የጦርነት ማስቆሚያ የመግባቢያ ስምምነት ሊባኖስንም እንደሚጨምር ይነገራል፡፡



በኒጀር ርዕሰ ከተማ ኒያሚ ትናንት በነበረው ከባድ የተኩስ ልውውጥ 35 ሰዎች ተገደሉ ተባለ፡፡


በኤርፖርቱ አቅራቢያ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እና ከባድ ፍንዳታ ነበር ተብሏል፡፡


ኢንዲያ ቱ ዴይ እንደፃፈው ከተገደሉት መካከል 22ቱ ጥቃት አድራሾች ናቸው ተብሏል፡፡



11 ወታደሮችም በተኩስ ልውውጡ እንደተሰውባቸው ሹሞች ተናግረዋል፡፡


በተኩስ ልውውጡ 2 ሰላማዊ ሰዎችም እንደተገደሉ ታውቋል፡፡


ኒጀር በቀጠናው የፅንፈኛ ታጣቂዎች ተፅዕኖ የበረታባት አገር ነች፡፡


በኒያሚ ኤርፖርት አቅራቢያ ከባድ ጥቃት ሲፈፀም ከ5 ወራት ባነሰ ጊዜ የትናንቱ 2ኛው ነው ተብሏል፡፡


ጥቃት ከፋቹ እኔ ነኝ ያለ ወገን የለም፡፡


የኒጀር ጎረቤቶች ማሊ እና ቡርኪናፋሶም የፅንፈኛ ታጣቂዎች ተፅዕኖ ያየለባቸው እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡



የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግዜስ በአውሮፓ የአሜሪካ ተጠባባቂ ሀይል የቆይታ ሁኔታ እንመረምረዋለን አሉ፡፡


የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሔግዜስ ጉዳዩን መመርመሩ በመንፈቅ ጊዜ እንደሚከናወን መናገራቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ፒት ሔግዜስ የአሜሪካ ወታደሮችን የአውሮፓ ቆይታ እንመረምረዋለን  ያሉት በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NETO) የመከላከያ ሹሞች ስብሰባ ወቅት ነው፡፡


የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር የኔቶ አባል አገሮች ላይ ነቀፋ እንደሰነዘሩ ተሰምቷል፡፡


ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራኑ ጦርነት ወቅት ከጎናችን አልቆሙም ባሏቸው የቃል ኪዳኑ አባል አገሮች ላይ ተደጋጋሚ ዘለፋ ሰንዝረዋል፡፡


ፒት ሔግዜስም የትራምፕን ነቀፋ መድገማቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡



የኔነህ ከበደ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page