top of page

ሚያዝያ 22፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለምዕራባዊያን አጋሮቻቸው አጣዳፊ የጦር መሳሪያ እርዳታችሁ ያሻናል አሏቸው፡፡


የአሜሪካ ሕግ አውጭዎች በቅርቡ ለዩክሬይን የ61 ቢሊዮን ዶላር የጦር መደገፊያ አፅድቀውላታል፡፡


ዜሌንስኪ የጦር መሳሪያ እርዳታው በፍጥነት ይላክልን ያሉት በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ጦራቸው በበርካታ ግንባሮች ማፈግፈጉ በተሰማበት ወቅት ነው፡፡


በምስራቃዊ ዩክሬይን የሩሲያ ጦር ተጨማሪ ቦታዎችን እየያዘ መሆኑን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የዩክሬይን ጦር ስለማፈግፈጉ የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ኦሌክሳንደር ሳርስኪዬ ጭምር ያረጋገጡት ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡


ዜሌንስኪ የሩሲያ ጦር ተጨማሪ መጠነ ሰፊ ማጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡



የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሐማስ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የተሰናዳውን ሰነድ እንደሚቀበል ተስፋ እናደርጋለን አሉ፡፡


ቢቢሲ እንደፃፈው ሰነዱ በጋዛ ሰርጥ ለ40 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡


በምላሹም ሐማስ ይዟቸው የሚገኙ ታጋቾችን በሙሉ እንዲለቅ የሚል አንቀፅ የሰፈረበት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ130 ያላነሱ ታጋቾች በሐማስ እጅ እንዳሉ ይነገራል፡፡


የሐማስ ልዑካን በዚህ ጉዳይ ከግብፅ እና ከካታር አደራዳሪዎች ጋር እየተናጋገሩ ነው ተብሏል፡፡


ሰነዱ ከተኩስ አቁም እና ከታጋቾቹ መለቀቅ በተጓዳኝ በጦርነቱ ምክንያት ከጋዛ ሰሜናዊ ክፍል ተፈናቅለው የሚገኙ ፍልስጤማውያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚጠይቅ ጭምር ነው ተብሏል፡፡


የጋዛው ጦርነት ወደ 7ኛ ወሩ እየተቃረበ ነው፡፡



አሜሪካ የሱዳንን ተፈላሚዎች ይረዳሉ ያለቻቸውን አገሮች ተፋላሚዎቹን መደገፋቸውን ሊያቆሙ ይገባል አለች፡፡


ጥሪውን ያቀረቡት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካዋ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስም በምህፃሩ RSF ለተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የጦር መሳሪያ በማቀበል ስሟ በሊንዳ ቶማስ ተነስቷል፡፡


ቀደም ሲል ኢሚሬትስ በሱዳን ለየትኞቹም ተፋላሚዎች መሳሪያ አላቀብልም ስትል አስተባብላለች፡፡


የአሜሪካዋ አምባሳደር ግን ሁለቱም ወገኖች የጦር መሳሪያ አቀባዮች አሏቸው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ውጊያ ከገጠሙ ከአመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡



በደቡብ ሱዳን የተከሰተው የተጣራ ነዳጅ እጥረት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱን ፈተና ላይ እንደጣለበት የአለም የምግብ ፕሮግራም እወቁልኝ አለ፡፡


ድርጅቱ ለእርዳታ ማጓጓዣነት በሚያስገባው ነዳጅ ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣሉ ለእጥረቱ ዋነኛው ምክንያት ነው ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


መንግስት ችግሩን አቃልላለሁ ቢልም እስካሁን በተግባር የታየ ነገር እንደሌለ የድርጅቱ የስራ ሀላፊዎች ተናግረዋል፡፡


በናይጀሪያም የተጣራ የነዳጅ ዘይት እጥረቱ በበርካታ ከተሞች ምጣኔ ሐብታዊ ክንውኑን እያወከው ነው ተብሏል፡፡


በእጥረቱ የተነሳም በአሁኑ ጊዜ በማደያ ጣቢያዎች ነዳጅ በቀላሉ እንደማይገኝ ተጠቅሷል፡፡


ብዙ አሽከርካሪዎችም ነዳጅ ለመቅዳት መኪኖቻቸውን ለበርካታ ሰዓታት በወረፋ ለማሳለፍ መገደዳቸው ተሰምቷል፡፡


መንግስታዊው ኩባንያ ግን በአገሪቱ የተጣራ ነዳጅ እጥረት አጋጥሟል መባሉን እያስተባበለ ነው፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





bottom of page