መጋቢት 16/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- Mar 25
- 2 min read
ለኢራን ጠቅላይ የደህንነት ምክር ቤት አዲስ የበላይ ተሰየሙ፡፡
የምክር ቤቱ የበላይ ሆነው የተሰየሙት ሞሐመድ ባጌር ዘልግ ሐድር እንደሆኑ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
የቀድሞው የምክር ቤቱ የበላይ ዓሊ ላርጃኒ ባለፈው ሳምንት በእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡

ላርጃኒን ተከትሎም የቀድሞው የደህንነት ሚኒስትርም ተገድለዋል፡፡
ከ3 ሳምንታት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አሙያቶላህ ዓሊ ሐሚኒን ጨምሮ በርካታ ሹሞች መገደላቸው ይነገራል፡፡
በጦርነቱ በአገሪቱ ከ1300 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል፡፡
ኢራንም በእስራኤል እና የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በሚገኙባቸው የአረብ አገሮች የአፀፋ የሚሳየል እና የድሮን ጥቃት እየሰነዘረች መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጦርነቱ ማብቂያ ጉዳይ ከኢራን ሹሞች ጋር ድርድር እየተካሄደ ነው አሉ፡፡
የኢራን ሹሞች በበኩላቸው ከአሜሪካ ጋር የተደረገ አንዳችም ንግግርም ሆነ ድርድር የለም እያሉ መሆኑ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ድርድር እየተካሄደ ነው መባሉን ሐሰተኛ ዜና ሲሉ ጠርተውታል የኢራን ሹሞች፡፡
ትራምፕ ከኢራን ሹሞች ጋር ድርድር እየተካሄደ ነው ቢሉም ከየትኞቹ ሹሞች ጋር እንደሆነ በስም ለይተው አልጠቀሱም፡፡
የጦርነት ማብቂያ ነው የተባለው ንግግር ጉዳይ አሁንም በውዥንብር እንደተሞላ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ መረጃ ለጦርነቱ ማብቂያ አሜሪካ ለኢራን ባለ 15 ነጥቦች የሰላም እቅድ ማቅረቧን ውስጥ አወቆች ነግረውኛል ብሎ ዎል ስትሪት ጆርናል ፅፏል፡፡
ሰነዱ ኢራን የኒኩሊር ተቋማቷን እንድታፈራርስ ጭምር የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡
እስከወዲያኛውም ዩራኒየም የተሰነውን ንጥረ ነገር በየትኛውም ደረጃ እንዳታብላላ የሚያስገድዳት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
የኢራን ሹሞች ግን ባለ 15 ነጥቦች ነው የተባለው ሰነድ እጃቸው ስለመግባቱ ያሉት ነገር የለም፡፡
የሊባኖስ መንግስት በአገሪቱ የኢራን አምባሳደር የነበሩትን ሞሐማድ ሬዛ ሼባኒን አገሬን ለቅቀው ይውጡኝ አላቸው፡፡
አምባሳደሩ ከትናንት በስቲያ ሊባኖስን ለቅቀው ይውጡ የተባሉት ኤምባሲው ከዲፕሎማሲያዊ ወግ ያፈነገጠ ተግባር እያከናወነ ነው በሚል ምክንያት እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የሊባኖሱ ሺአ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ መንግስት የኢራኑን አምባሳደር ለማባረር መወሰኑን አጥብቆ መቃወሙ ተሰምቷል፡፡
ሔዝቦላህ የሊባኖስን መንግስት እርምጃ የኃያላን አገሮች ተፅዕኖ ውጤት ነው ብሎታል፡፡
ሔዝቦላህ በቀደመው ጊዜ ከተሰሚነትም በላይ በሊባኖስ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ሀያል እንደነበር ይነገራል፡፡
የኢራንም ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ አጋር ነው፡፡
የሊባኖስ መንግስት በአገሩ የነበሩትን የኢራን አምባሳደር ከማባረርም በላይ በኢራን የነበሩትን አምባሳደሩን ወደ አገር ቤት እንዳስጠራቸው መረጃው አስታውሷል፡፡
አንድ ጃፓናዊ የጦር መኮንን በቶኪዮ በሚገኝ የቻይና ኤምባሲ ግንቡን ተንጠላጥሎ በመዝለል ወደ ግቢው መዝለቁ ቻይናን ክፉኛ አስቆጣት፡፡
ቻይና በጃፓናዊው የጦር መኮንን ድርጊት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ አማካይነት ብርቱ ተቃውሞዋን እንዳሰማች አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ጃፓናዊው የጦር መኮንን በቶኪዮ በሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ግንብ ዘልሎ ወደ ውስጥ የዘለቀው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጣሙን ሻክሮ በሚገኝበት አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡
ግለሰቡ ወደ ኤምባሲው ግቢ ግንብ ዘልሎ ከገባ በኋላ መያዙ ተሰምቷል፡፡
ይሁንና የጃፓን ፖሊስ በዚህ ጉዳይ ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥቧል ተብሏል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሹሞች ጉዳዩ በብርቱ እንዲመረመርላቸው መጠየቃቸው ታውቋል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments