top of page

ጥቅምት 8፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


የጊኒ ቢሳዎ ርዕሰ ከተማ ኤሌክትሪክ በመቋረጡ በድቅድቅ ጨለማ መዋጧ ተሰማ፡፡


ቢሳዎ በጨለማ የተዋጠችው የአገልግሎት ዋጋዬ አልተከፈለኝም ያለ የቱርክ ኩባንያ አገልግሎት በማቋረጡ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ኩባንያው ለቢሳዎ ኤሌክትሪክ ሲያቀርብ የቆየው ከተንሳፋፊ የመርከብ የሀይል ማመንጫ ነው ተብሏል፡፡


እንደሚባለው የቱርኩ ኩባንያ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ያቋረጠው 15 ሚሊዮን ዶላር ስላልተከፈለው ነው፡፡


በኤሌክትሪክ መቋረጡ የተነሳ ሆስፒታሎች ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ሌሎችም የአገልግሎት መስጫዎች ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡


የቱርኩ ኩባንያ ለበርካታ የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የናይጀርያ ፖሊስ በንግድ ማዕከሏ ሌጎስ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ስፍራን ያዝኩ አለ፡፡


ድብቅ ሆኖ የቆየው ፋብሪካ እንደ ጠመንጃ ፣ ሽጉጥ እና መሰል ጥይቶች ሲመረቱበት መቆየቱን ቢቢሲ የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሶ ፅፏል፡፡


ናይጀርያ በህገ-ወጥ ታጣቂዎች ከፍተኛ የፀጥታ ችግር የተጋረጠባት አገር ነች፡፡


የማስለቀቂያ የቤዛ ክፍያ ፍለጋ ተብሎ የሚፈፀም የሰዎች እገታም እየተደጋገመባት ነው፡፡


ፖሊስ በሌጎሱ ድብቅ የጦር መሳሪያዎች ማምረቻ በርካታ አውቶማቲክ የክላሺንኮቭ ጠመንጃዎችን ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡




ሳውዲ አረቢያ በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቿ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ጠየቀች፡፡


ሳውዲ ዜጎቿ ሊባኖስን ለቅቀው እንዲወጡ የመከረቻቸው በሊባኖስ እና በእስራኤል ወሰን ውጥረት እየተካረረ በመምጣቱ እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


ቀደም ሲል በእስራኤል ጦር እና ሔዝቦላህ በተሰኘው የሊባኖስ የጦር ድርጅት መካከል የከባድ መሳሪያ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ዘገባው አስታውሷል፡፡


እስራኤል እና ሔዝቦላህም ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ፡፡


በቤይሩት የሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩት ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡


ሔዝቦላህ የኢራን ጥብቅ ወዳጅ እና አጋር መሆኑ ይነገራል፡፡



የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚፈፅመውን ድብደባ በመቃወም በመላው የኢራን ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ፡፡


በተለይም ከትናንት በስቲያ በጋዛ በአንድ ሆስፒታል ላይ በደረሰ ፍንዳታ ከ500 ያላነሱ ፍስጤማውያን መገደላቸው በኢራን ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡


እስራኤል ድብደባውን ፈፅማለች ብትባልም እሷ ግን በሆስፒታሉ ፍንዳታ የደረሰው ኢስላማዊ ጂሃድ በስህተት በተኮሰው ሮኬት ነው ማለቷን አናዶሉ ፅፏል፡፡


በኢራን በጋዛው የሆስፒታል ድብደባ ለተገደሉት ፍልስጤማውያን የ1 ቀን ብሔራዊ ሐዘን መታወጁ ታውቋል፡፡


የኢራኑ ፕሬዘዳንት ኢብራሂም ራይሲ የሞስሊም አገሮች የእስራኤልን የጋዛ ድብደባ ለማስቆም ሀይላቸውን ሊያስተባብሩ ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የእስራኤል መንግስት ለሰላማዊ ፍልስጤማዊያን ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ መግባቱን አልቃወምም አለ፡፡


ብቻ እርዳታው በጭራሽ ለሐማስ መድረስ የለበትም ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የእስራኤል መንግስት ወደ ጋዛ ሰርጥ ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ መፍቀዱን እወቁልኝ ያለው የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በእስራኤል ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡


ቀደም ሲል እስራኤል ወደ ጋዛ ምግብ ፣ ውሃ እና ነዳጅ እንዳይገባ ከልክላ መሰንበቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡


በፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት /ሐማስ/ እና በእስራኤል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በጋዛ ሰርጥ ከሚሊዮን ያላነሱ ፍስጤማውያን መፈናቀላቸው ይነገራል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

bottom of page