ጥቅምት 7 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Oct 17
- 2 min read
የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሕንድ የሩሲያን የነዳጅ ዘይት መግዛት እንደምታቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራሞዲ ማረጋገጫ ሰጥተውኛ ስለማለታቸው የምናውቀው ነገር የለም አለ፡፡
ትራምፕ ከትናንት በስቲያ ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ መግዛት እንደምታቆም ማረጋገጫ አግኝቻቸው ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡

የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ በትራምፕ እና በናሬንድራ ሞዲ መካከል ይህን መሰል ንግግር ስለመደረጉ አላውቅም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከዚህ ቀደም ንግግረግ ቢደረግም ነዳጁ ግዢውን ስለማቆም የተደረሰ መደምደሚያ የለም ብለዋል፡፡
የህንድ መንግስት በዚህ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ እኛ የምናስቀድመው የአገሪቱን ፍላጎት እና የኢነርጂ ዋስትና ነው ማለቱ ተጠቅሷል፡፡
ሕንድ ከቻይና በመቀጠል 2ኛዋ ታላቅ የሩሲያ የነዳጅ ዘይት ገዢ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬይኑ ጦርነት መቆሚያ ጉዳይ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሐንጋሪ ቡዳፔስት ዳግም የገፅ ለገፅ ንግግር ሊያደርጉ ነው፡፡
የመሪዎች የገፅ ለገፅ ንግግር በሐንጋሪ ቡዳፔስት እንደሚዳረግ ትራምፕ በትሩዝ ማህበራዊ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት እወቁልኝ ማለታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የሩሲያ ሹሞችም የትራምፕ እና የፑቲን ንግግር በቡዳፔስት እንደሚደረግ ማረጋገጫ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዛሬ የዩክሬይኑን ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን በዋይት ሐውስ ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ ታውቋል፡፡
የትራምፕ እና የፑቲን የቡዳፔስት ንግግር ይከናወናል ቢባልም መቼ እንደሆነ ግን የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
የቡዳፔስቱ ንግግር የተወጠነው ሁለቱ መሪዎች ትናንት ለሁለት ሰዓታት የዘለቀ የስልክ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ያደረጉትን የስልክ ውይይት ፍሬያማ ነበር ማለታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
የየመን ሁቲዎች ከፍተኛ የጦር አዛዣቸው ሜጀር ጄኔራል ሞሐመድ አል ጋማሪ መገደላቸውን በይፋ ተናገሩ፡፡
አል ጋማሪ በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ሁቲዎቹ በይፋዊ መግለጫው እንደጠቀሱ TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡
መግለጫው አል ጋማሪ የተገደሉበትን ቀን አላነሳም፡፡
እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ባካሄደችባቸው 2 ዓመታት ሁቲዎቹም በእስራኤል ላይ የሚሳየል እና የድሮን ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል፡፡
የሁቲዎቹ መግለጫ አል ጋማሪ ከ13 አመት ወንድ ልጃቸው ጋር ነው የተገደሉት ብሏል፡፡
እስራኤልም በሁቲዎቹ ይዞታ ላይ ተደጋጋሚ ከባድ የአየር እና የሚሳየል ጥቃቶችን ማድረሷ በተደጋጋሚ የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡
ሁቲዎቹ ከእስራኤል ጋር ጦርነታችን ገና አላበቃም ብለዋል፡፡
ለአል ጋማሪ ግድያ እስራኤልን እንበቀላታለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ከእስራኤል በኩል የተሰጠ ምላሽ በዘገባው አልተጠቀሰም፡፡
ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ ሁነኞቹ የኢራን የጦር እና የፖለቲካ አጋሮች ናቸው፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የሱዳኑ የኮሌራ ወረርሽኝ መዛመት በእጅጉ አሳስቦኛል አለ፡፡
በአገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ መዛመት ከያዘ ከአመት በላይ እንደሆነው አፍሪካ ኒውስ አስታውሷል፡፡
በዚህ ጊዜ ከ120,000 በላይ ሱዳናውያን በበሽታው ሲያዙ የ3400 ያህል ሰዎች ሕይወት አልፏል ተብሏል፡፡
ወረርሽኙ በአሁኑ ሰዓት ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የወረርሽኙ በጣሙን መዛመት በእጅጉ አሳስቦኛል ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ከ2 አመት ከመንፈቅ በላይ በጦርነት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments