top of page

ጥቅምት 6 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 7 days ago
  • 3 min read

የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ የተደረገባትን ማዳጋስካርን ከአባልነት አግጃለሁ ማለቱ ተሰማ፡፡


በዚያ ካፕሳት የተሰኘው ልዩ የጦር ክፍል መኮንኖች የፕሬዘዳንት አንድሬይ ራጆሊናን መንግስት ማስወገዳቸውን እወቁልን ያሉት መሰንበቻው እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡

ree

የጦር መኮንኖቹ መንግስታዊ ስልጣኑን የተቆጣጠሩት አገሪቱ ከ2 ሳምንታት በላይ በተቃውሞ ስትናጥ ከሰነበተች በኋላ ነው፡፡


የአገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት የገልባጮቹ አለቃ ኮሎኔል ሚካኤል ራንድ ኒሪያናን ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት እንዲሆኑ ፈቅዶላቸዋል፡፡


የገልባጮቹ አለቃ በነገው እለት ቃለ መሐላ በመፈፀም ሀላፊነታቸው ይረከባሉ ተብሏል፡፡


ከዚያ አስቀድሞ ግን የአፍሪካ ህብረት ማዳጋስካርን ከአፍሪካ ህብረት አባልነትዋ አግጃለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡



የቬኒዙዌላው ፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት(CIA) አማካይነት የመንግስት ግልበጣ እየቶደለተብኝ ነው አሉ፡፡


ማዶሮ በ CIA አማካይነት መፈንቅለ መንግስት ሊደረግብኝ እየተሴረ ነው ያሉት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገራቸው ጦር የቬኒዙዌላን የአደገኛ ዕጽ አስተላላፊዎች ለመደምሰስ በምድር ጥቃት እንደሚከፍት ፍንጭ ከሰጡ በኋላ እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡


የአሜሪካ ጦር በቅርቡ በካሪቢያን ደቡባዊ ክፍል መነሻቸው ከቬኒዙዌላ የሆነ አራት ጀልባዎችን ሲያወድም በጥቂቱ 27 ሰዎችን መግደሉ ሲነገር ቆይቷል፡፡


የአሜሪካ ጦር አሰማኝ ማስረጃ ባያቀርብም ጀልባዎቹን ያወደምኳቸው አደገኛ እጽ ጭነው ወደ አሜሪካ ሲያመሩ ነው ብሏል፡፡


የቬኒዙዌላው ፕሬዘዳንት አሜሪካ አደገኛ ዕፅ አስተላላፊዎችን በመዋጋት ሽፋን የሥርዓት ለውጥ ለማስከተል ያለመ ወረራ ልትፈፅምብን እያሴረች ነው ሲሉ ተናግረዋል በተደጋጋሚ፡፡


አሜሪካ ማዱሮንም በአደገኛ እፅ አስተላላፊ የተደራጀ የወንጀል ቡድን መሪነት እየከሰሰቻቸው ነው፡፡


እሳቸውን ይዞ ለማሰር ለሚያግዙኝ የ50 ሚሊዮን ዶላር ወረታ እከፍላለሁ ካለች ሰንብታለች፡፡


ማዱሮም አሜሪካ በቬኒዙዌላ ላይ ትፈፅመዋለች ያሉትን ወረራ ለመከላከል የበኩላቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡



የኬንያው ፕሬዘዳንት ዊልያም ሩቶ በአገሪቱ የቀድሞ የብሔራዊ እርቅ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ሕልፈት ምክንያት የ7 ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አወጁ፡፡


ኦዲንጋ ባጋጠማቸው የልብ ህመም ለህክምና በሄዱባት ሕንድ በ80 አመታቸው ማረፋቸው የተሰማው ትናንት እንደሆነ TRT ፅፏል፡፡


ፕሬዘዳንት ሩቶ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቀብር መንግስታዊ ክብር እንደሚቸረው ተናግረዋል፡፡


በኦዲንጋ ሕልፈት ምክንያት የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ሲውለበለሰብ እንደሚሰነብት ታውቋል፡፡


ራይላ ኦዲንጋ ከ12 አመታት በፊት የኬኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡


ባይሳካላቸውም ለ5 ጊዜያት በፕሬዘዳንታዊ ተፎካካሪነት ቀርበው ነበር፡፡


ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበርነት ከተፎካካሩት መካከል አንዱ እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡



የጋና መንግስት ከአሜሪካ ተባራሪ የ3ኛ አገር ስደተኞችን መቀበሉን በተመለከተ በአገር በቀል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፋይል ተከፈተበት፡፡


የአገሪቱን መንግስት በዚሁ ጉዳይ ችሎት ለመገተር ፋይል የተከፈተበት ዲሞክራሲ ሐብት በየተሰኘ አገር በቀል ድርጅት እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡


አሜሪካ ወደ ጋና ያባረረቻቸው የ3ኛ አገሮች ስደተኞች ብዛት 42 ደርሷል ተብሏል፡፡


በጋና መንግስት ላይ የክስ ፋይል የከፈተው ድርጅት መንግስት ተባራሪ ስደተኞችን መቀበሉ አለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የአገሪቱን ህገ መንግስትም የሚጋፋ ነው ብሎታል፡፡


ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ 47ኛ ፕሬዘዳንት ከሆኑ በኋላ አስተዳደራቸው ህገወጥ ናቸው ያላቸውን ስደተኞች በገፍ በማባረሩ እንደገፋበት ይነገራል፡፡


ተባራሪዎቹን የ3ኛ አገር ስደተኞች መቀበል ከጀመሩት የአፍሪካ አገሮች መካከል ጋና 1 ኢስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን የተወሰኑት እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡



የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን በከበባ ውስጥ ያለችው የኤልፋሽር ከተማ ነዋሪዎች ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ በእጅጉ አሳስቦኛል አለ፡፡


የሰሜን ዳርፉሯ ማዕከል ኤል ፋሸር ከተማ በRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ከበባ ውስጥ ከገባች ቆይታለች፡፡


የከተማዋ ምግብ በመሟጠጡ ነዋሪዎቿ የረሃብ ስጋት እንደተጋረጠባቸው አናዶሉ ፅፏል፡፡


በየገበያውም የሚሸጥ እና የሚገዛ የለም፡፡


ወደ ከተማዋ ሰብአዊ እርዳታ ማስገባት ከማይቻልባት ደረጃ ተደርሷል ተብሏል፡፡


በንጹህ ውሃ እጦት የተነሳ ከ120 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች መጋለጣቸው ተጠቅሷል፡፡


በዚህም የተነሳ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ (ኦቻ) የኤል ፋሽር ነዋሪዎች ያሉበት በጣሙን አስቸጋሪ ሁኔታ በእጅጉ አሳስቦኛል ማለቱን መረጃው አስታውሷል፡፡



የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት /ሐማስ/ ትጥቅ እንዲፈታ በብርቱ አስጠነቀቁት ተባለ፡፡


ኔታንያሁ በጋዛ የተኩስ አቁም ያደረግነው ለሰላም እድል ለመስጠት ነው ማለታቸውን CBS ፅፏል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐማስ አንድም ነገር ሳያስቀር ትጥቁን ማስረከብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡


የኔታንያሁ ማስጠንቀቂያ ካለበለዛም አለበት፡፡


ኔታንያሁ ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ ካልሆነ ጋዛን ገሐነበ እሳተ እናደርግበታለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የሐማስ ትጥቅ መፍታት ጉዳይ የቀጣዩ ድርድር ርዕሰ ጉዳይ እንደሚሆን ሲነገር ሰንብቷል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዛ ሰርጥ ዘላቂ ሰላም ባቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች እቅድ ይሄ ጉዳይ መነሳቱን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page