top of page

ጥቅምት 29 2018 - ጥቅምት 29 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 28 minutes ago
  • 1 min read

 

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የቡድን 20 አባል አገሮች ጉባኤ አይገኝም አሉ፡፡

 

የአሜሪካውፕሬዘዳንት አፍሪካ ነርስ በተሰኙት ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን ላይ እልቂት እና ማሳደዱ በርትቶባቸዋል የሚል ክሳቸውን እየደጋገሙት መሆኑን አናዶሉ አስታውሷል፡፡

 

ree

የፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ መንግስት በትራምፕ የሚቀርበውን ውንጀላ በተደጋጋሚ እያስተባበለ ነው፡፡

 

ትራምፕ ግን የደቡብ አፍሪካን መንግስት ጥምድ አድርገው እንደያዙት ነው፡፡

 

እንደውም ደቡብ አፍሪካ ከቡድን 20 አባል አገርነቷ ልትባረር ይገባል ያሉት ሰሞኑን ነው፡፡

 

የቡድን 20 አባል አገሮች ስብሰባ በደቡብ አፍሪካ ቢካሄድም ያለ አሜሪካ ተሳትፎ ይሆናል ተብሏል፡፡

 

 

በምዕራብ አፍሪካዊቱ ሀገር ማሊ 5 ሕንዳውያን መታገታቸው ተሰማ፡፡

 

ሕንዳውያኑ በታጠቁ ሰዎች የታገቱት በምዕራባዊ ማሊ እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡

 

እስካሁንም ሕንዳውያኑን ያገትኩት እኔ ነኝ ያለ ወገን እንደሌለ ተጠቅሷል፡፡

 

ማሊ የተለያዩ ፅንፈኛ ታጣቂዎች የገነኑባት አገር እንደሆነች በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

 

5 ሰራተኞቹ የታገቱበት ኩባንያ የተቀሩትን ወደ ርዕሰ ከተማዋ በማኮ ለመላክ መገደዱ ተሰምቷል፡፡

 

ምዕራብ አፍሪካዊቱ አገር ፀጥታዋ ከደፈረሰ በርካታ አመታት ማስቆጠሯን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

ኢራን በሜክሲኮ የእስራኤሉን አምባሳደር ለማስገደል አሲራ ነበር መባሉን በፍጹም ሐሰት ነው አለች፡፡

 

ኢራን በሜክሲኮ የሚገኙትን የእስራኤሉን አምባሳደር ለማስገደል አሲራ ነበር የሚል ክስ ያቀረቡት አሜሪካ እና እስራኤል እንደሆኑ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡

 

በሜክሲኮ የኢራኑ አምባሳደር ግን የእስራኤል እና የአሜሪካን ክስ የመገናኛ ብዙሃን ወሬ ማሟሟቂያ ነው ብለው መጥራታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ኢራን በኒኩሊየር መርሐ ግብሯ የተነሳ ከአሜሪካ ጋር በፍጹም ጠላትነት የምትተያይ አገር ነች፡፡

 

እስራኤልም ባለፈው አመት ሰኔ ወር ከኢራን ጋር ወደ ከባድ ግጭት አምርታ እንደነበር ይታወቃል፡፡

 

አሜሪካ እና እስራኤል ስለ ሴራው ባነሱት ጉዳይ የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማውቀው ነገር የለም ማለቱ ተሰምቷል፡፡

 

 

በታንዛኒያው የምርጫ ሰሞን ብጥብጥ ወቅት ከተያዙት መካከል 76ቱ በአገር ክህደት ክስ ተመሰረተባቸው ተባለ፡፡

 

አወዛጋቢነት ባላጣው ፕሬዘዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን 98 በመቶ ያህሉን ድምፅ አግኝተዋል ተብለው አሸናፊ መደረጋቸውን አፍሪካ ኒውስ አስታውሷል፡፡

 

ሳሚያ ሁሉሁ ያሸነፉት ሁነኛ የተቃዋሚ ተፎካካሪዎች በምርጫው እንዳይሳተፉ በተደረገበት አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡

 

በዚህም የተነሳ ከድምፅ መስጫው እለት አንስቶ የተቃዋሚዎች ደጋፊዎች የተቃውሞ ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል፡፡

 

ከፀጥታ ሀይሎችም ጋር ከባድ ግጭት አድርገው በመቶዎች የሚቆጠሩት ተገድለዋል ተብሏል፡፡

 

አሁን በብጥብጡ ወቅት ከተያዙት የተቃውሞ ሰልፈኞች መካከል 76ቱ በአገር ክህደት ክስ እንደተመሰረተባቸው ተሰምቷል፡፡

 

#ሰሜን ኮሪያ

 

ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ የባልስቲክ ሚሳየል ከመሞከር አልመለስም አለች፡፡

 

የሰሜን ኮሪያ አቋም የተሰማው የሰሞኑን ቀዳሚ ሙከራዋ በደቡብ ኮሪያ እና በአሜሪካ መወገዙን ተከትሎ እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

መሰንበቻውን ሰሜን ኮሪያ የባልስቲክ ሚሳየል ሙከራዋን እየደጋገመች ነው፡፡

 

ተጨማሪ ሙከራዎችን ባደርግስ ማን አለኝ ከልካይ ብላለች ሰሜን ኮሪያ፡፡

 

ሰሜን ኮሪያ በቀጠናው ከደቡብ ኮሪያ ጋር ባልተቋረጠ የጦር ፍጥጫ ላይ ትገኛለች፡፡

 

አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እንዳሏት መረጃው አስታውሷል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page