ጥቅምት 25 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 3 minutes ago
- 2 min read
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ አገሬ ከአሜሪካ ጋር ወደ ኒኩሊየር ነኩ ንግግር ለመመለስ የሚያጣድፉት ጉዳይ የለም አሉ፡፡
አርጋቺ ከአሜሪካ ጋር በእኩልነት ደረጃ ካልሆነ በስተቀር አንዳችም ንግግር ማድረግ እንደማትሻ መናገራቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡

አሜሪካ ኢራን በጭራሽ ዩራኒየም ማብላላት የለባትም የሚል አቋም አላት፡፡
አዲሱ የአሜሪካ የንግግር ሀሳብም በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ነው ይባላል፡፡
ኢራን ደግሞ ይሄን በጭራሽ አልቀበልም ባይ ነች፡፡
ምዕራባዊያኑ ኃያላን ኢራን የኒኩሊየር ቦምብ የመስራት ውጥን አላት ሲሉ ይከሷታል፡፡
ቴሕራን በበኩሏ የኒኩሊዩር መርሐ ግብሬ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እና ለሰላማዊ አገልግሎት የታለመ ነው የሚል መሟገቻ ታቀርባለች፡፡
ፔሩ ከሜክሲኮ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች፡፡
ፔሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ያቋረጠችው ከ3 አመታት በፊት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በማድረግ ለተከሰሱት የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤትሲ ቻቬዝ ሜክሲኮ ጥገኝት በመፍቀዷ ምክንያት ነው መባሉን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ሴትዮዋ በፔሩ ሊማ በሚገኘው የሜክሲኮ ኤምባሲ ተጠልለው እንደሚገኙ ይነገራል፡፡
የፔሩ መንግሰት ሜክሲኮ ለቤትሲ ቻቬዝ ጥገኝነት መፍቀዱ በእጅጉ አሳዝኖኛል ማለቱ ተሰምቷል፡፡
እርምጃውንም ፍጹም የጠላትነት ተግባር ነው ሲል ጠርቶታል፡፡
በዚህ ጉዳይ ከሜክሲኮ በኩል የተሰማ አስተያየት የለም ተብሏል፡፡
የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በእጅጉ ከደፈረሰበት ደረጃ መድረሱ ይነገራል፡፡
አሜሪካ የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ሙከራ እንዳታደርግ በቻይና ተጠየቀች፡፡
የቻይናን ጥያቄ ያቀረቡት የእስያዊቱ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ ማኦ ኒንግ እንደሆኑ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ወደ ኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ሙከራዋ እንድትመለስ ያዘዙት በቅርቡ ነው፡፡
ትራምፕ እንደ ሩሲያ እና ቻይና ያሉ አገሮች ከምድር በታች ሚስጥራዊ የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ሙከራ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
የቻይናዋ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይዋ ግን እኛ በጭራሽ ሙከራ አላደረግንም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የሩሲያ ሹሞችም ቀደም ሲል ወደ ኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ሙከራ እንዳልተመለሱ ተናግረዋል፡፡
ኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ባለቤት አገሮቹ በጋራ መግባባት ሙከራውን ማድረግ ካቆሙ ከ30 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል ይባላል፡፡
የጊኒው ወታደራዊ መንግስት መሪ ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ በመጪው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሊፎካከሩ ነው፡፡
ኮሎኔሉ በእጩነት ለመቅረብ ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማመልከቻ ማስገባታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ማማዲ ዱምቦያ በወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ የአገር መሪ ከሆኑ 4 ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡
ኮሎኔሉ ከ4 አመታት በፊት የፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴን መንግስት እንደገለበጡ እሳቸውም ሆኑ የግልበጣ ጓደኞቻቸው የሽግግሩ ጊዜ ሲያበቃ ስልጣን በሕዝብ ለተመረጠ እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተው ነበር፡፡
የጊኒው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ከወር በኋላ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡
በጊኒ ለፕሬዘዳንታዊ ምርጫው በእጩነት የሚቀርቡ ግለሰቦች በነፍስ ወከፍ የ100 ሺህ ዶላር የምንዛሪ ግምት ያለው ገንዘብ ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል የተባለው በቅርቡ ነው፡፡
ይህም እርምጃ አገሩን በእጅጉ ማስደንገጡ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








