top of page

ጥቅምት 19፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


ወደ ኬንያ የሚመጡ አፍሪካዊያን በሙሉ ቪዛ መጠየቁ ሊቀርላቸው ነው ተባለ፡፡


የኬንያው ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ወደ ኬኒያ ለሚመጡ አፍሪካዊያን ቪዛ መጠየቁ እንደሚቀር በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደ የአየር ለውጥ መገደቢያ ጉባኤ ወቅት መናገራቸውን ዘ ስታር ፅፏል፡፡


ከአንዷ የአፍሪካ ሀገር ወደ ሌላዋ በሚደረግ ጉዞ ቪዛን ማስቀረቱ የአፍሪካ ህብረት ነባር ውጥን እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡


በዚህ ረገድ አባል ሀገሮቹ በአሁኑ ወቅት መልካም እርምጃ እያሳዩ ነው ተብሏል፡፡


ቀደም ሲል ሲሼልስ ፣ ጋምቢያ እና ቤኒን ሁሉም አፍሪካዊያን ያለ ቪዛ እንዲገቡ የፈቀዱ ሀገሮች እንደሆኑ ለትውስታ የጠቀሰው ደግሞ ሉሳካ ታይምስ ነው፡፡


እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ በአፍሪካ ሀገሮች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ ምጣኔ ሐብታዊ ትፋፋቱም የበዛ ነው ተብሏል፡፡




የጋዛ የቀይ ጨረቃ ማህበር የአል ኩድስ ሆስፒታልን ሙሉ በሙሉ ለቀን እንድንወጣ በእስራኤል ታዘናል አለ፡፡


በሆስፒታሉ በፅኑ ሕሙማን ክፍሎች የሚገኙት ታካሚዎችን ይዞ መውጣትም ሆነ ትቶ መሄዱ የማይሞከር ነው ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በማሞቂያ ክፍሎችም በርካታ ጨቅላዎች በመኖራቸው ከዚያ መልቀቁ የማይሆን ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡


በእዚያ ላይ ሆስፒታሉ የ14,000 ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች መጠለያ እንደሆነም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


ትናንት ቀኑን ሙሉ የሆስፒታሉ አቅራቢያ በእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ሲደበደብ ነበር ተብሏል፡፡


ሐማስ ከ3 ሳምንታት በፊት ወደ እስራኤል በመዝለቅ ለ1,400 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነ ድንገት ደራሽ ጥቃት ካደረሰ ወዲህ የእስራኤል ጦር ጋዛን ያለፋታ እየቀጠቀጠው ነው፡፡


በእስራኤል የአፀፋ ጥቃት የተገደሉት ፍልስጤማዊያን ብዛት ከ8,000 መብለጡ ተሰምቷል፡፡



የሱዳን ተፋላሚዎች የሰላም ንግግር ቀጥሏል ተባለ፡፡


ተፋላሚዎቹ ለወራት ተቋርጦ የቆየውን የሰላም ንግግራቸውን በሳውዲ አረቢያ ጄዳ ዳግም የቀጠሉት ባለፈው ሳምንት እንደሆነ አፍሪካ ኒውስ አስታውሷል፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ከመንፈቅ በላይ በጦርነት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡


በቀዳሚው የሰላም ንግግራቸው በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ቢደርሱም አንዱም በተግባር ሳይውል ተጨናግፎ ቀርቷል፡፡


የሱዳኑ ጦርነት እስካሁን ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፎበታል፡፡


6 ሚሊዮን ያህሉን ደግሞ ለስደት እና መፈናቀል መዳረጉ ይነገራል፡፡


በአሜሪካ ሪፖብሊካዊ የፖለቲካ ማህበሩን ወክለው በፕሬዘዳንታዊ እጩነት ለመቅረብ የሚፎካከሩት ፖለቲከኞች በጦርነት ላይ ላለችው እስራኤል ድጋፋችን ወሰን አይኖረውም አሉ፡፡


የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወዳጅ ሀጋራችን የሆነችውን እስራኤልን ከማንም በላይ እንጠብቃታለን ማለታቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


የፍሎሪዳው ገዢ ሮን ዴሳንቲስም እስራኤልን በመደገፍ ሞቅ ያለ ንግግር ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡


የሪፖብሊካው የፖለቲካ ማህበር የፕሬዘዳንታዊ እጩ ተፎካካሪዎች እስራኤልን በመደገፍ ንግግር ያደረጉት በአሜሪካ ተፅዕኖ አሳዳሪ የአይሁድ ማህበረሰብ ወኪሎች ስብሰባ ወቅት መሆኑ ታውቋል፡፡


ይህ በዚህ እንዳለ የቀድሞው ምክትል ፕሬዘዳንት ማይክ ፔንስ በእጩነት ለመቅረብ ከገባሁበት ፉክክር መውጣቴን እወቁልኝ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

bottom of page