ጥቅምት 12 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 9 hours ago
- 2 min read
በካሜሩን ከሳምንት በፊት በተካሄደው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አረጋዊው የአገሪቱ መሪ ፖል ቢያ እንዳሸነፉ የቅድሚያ ውጤቱ አሳየ ተባለ፡፡
የአገሪቱ የምርጫ አከናዋኝ መስሪያ ቤት በቅድሚያ ውጤቱ ፖል ቢያ ለፕሬዘዳንታው ምርጫው ከተሰጠው ድምፅ 53 በመቶውን በማግኘት አሸንፈዋል ማለቱን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
የፖል ቢያ የቅርብ ተፎካካሪ ኢሳ ቺሮማ ባካሪ ያገኙት ድምፅ 35 በመቶ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ባካሪ ከምርጫው በኋላ በተደጋጋሚ አሸንፌያለሁ ሲሉ ሰንብተዋል፡፡
ኢሣ ቺሮማ ባካሪ ውጤቱ በወጉ ይጣራልኝ ማለት መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡
የ92 አመቱ አረጋዊ ፖል ቢያ የምርጫ ድላቸው ከፀናላቸው የ42 አመታት መሪነታቸውን በመ5 ዓመታት ይጨምርላቸዋል ተብሏል፡፡
የአገሪቱ ህገ መንግስታዊ ምክር ቤት ይፋዊ ውጤቱን ሰሞኑን እወቁት እንደሚል በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
በናይጀሪያ ኒጀር ግዛት በአንድ የነዳጅ ማጓጓዣ ቦቴ ባጋጠመው ፍንዳታ በጥቂቱ የ38 ሰዎች ሕይወት አለፈ ተባለ፡፡
ከፍንዳታው አስቀድሞ የነዳጅ ማጓጓዣው እንደተገለበጠ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡
ቦቴው እንደተገለበጠ የአካባቢው ነዋሪዎች በየጀሪካኑ ከነዳጅ ማጓጓዣው ነዳጅ ለመቅዳት ሲረባረቡ ፍንዳታው መድረሱ ታውቋል፡፡
በመጥፎው አጋጣሚ ሕይወታቸው ካለፈው ሌላ በርካቶች ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ተጠቅሷል፡፡
አደጋው ተሽከርካሪዎች በሚበዙበት የፍጥነት መንገድ በማጋጠሙ የሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉ ተሰምቷል፡፡
በናይጀሪያ መሰል የነዳጅ ማጓጓዣዎች ፍንዳታ እንደሚደጋገም መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ጋዛ የአለም አቀፉን አረጋጊ ሀይል ወታደሮች የሚያዋጡት የመካከለኛው ምስራቅ እና የአካባቢው አገሮች ናቸው አሉ፡፡
ትራምፕ አረጋጊው ሀይል የፍልስጤማዊው ታጣቂ ቡድን የሰላም ሂደቱን አውካለሁ ካለ ልክ ያስገባዋል ሲሉ በትሩዝ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንደፃፉ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
አረጋጊው ሀይል የውጊያ ተልዕኮም እንደሚኖረው ፍንጭ ሰጥተዋል ትራምፕ፡፡
የትራምፕ ባለ 20 ነጥቦች የሰላም እቅድ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እና በወደፊቱም የጋዛ አስተዳደር ድርሽ እንዳይል ይጠይቃል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሐማስ ጋር የተደረገ ድርድርም ሆነ የተደረሰ ስምምነት የለም፡፡
የጋዛ አረጋጊዎችን በመላክ ኢንዶኔዥያ ስሟ በዘገባው ተነስቷል፡፡
ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአካባቢው አገሮች ለጋዛው ተልዕኮ ሰራዊት ያዋጣሉ ቢሉም ለጊዜው ሰራዊት የሚያዋጡትን አገሮች በስም እንዳልጠቀሱ መረጃው አስታውሷል፡፡
በኢራን አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የጦር ክፍል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሞሐመድ ፓክፑር በአገራችን ላይ አንዳች ጥቃት ከተሰነዘረባት ቀጠናውን ገሐነመ እሳት እናደርጋለን ሲሉ ዛቱ፡፡
ኢራን ባለፈው አመት ሰኔ ወር በኒኩሊየር መርሐ ግብሯ መነሻ ከእስራኤል ጋር ለ12 ቀናት ከባድ ግጭት ውስጥ ገብታ እንደነበር ኢራን ኢንተርናሽናል አስታውሷል፡፡
በጊዜው ወደ ጦርነቱ ማብቂያ አሜሪካም የኢራንን ታላላቅ የኒኩሊየር ተቋማት በB 52 ቦምብ ጣዮች መምታቷ ይታወቃል፡፡
የኢራኑ ከፍተኛ የጦር መኮንን ዳግም ጥቃት የሚሰነዘርብን ከሆነ ምላሻችን ከዚያን ጊዜው የከፋ ይሆናል ብለዋል፡፡
የሜጀር ጄኔራል ፓክፑር አስተያየት የተሰማው ከኢራቁ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ምዕራባዊያን ኃያላን እና እስራኤል ኢራን የኒኩሊየር ቦምብ የመታጠቅ ውጥን አላት ሲሉ ይከሷታል፡፡
ኢራን ግን የኒኩሊየር መርሐ ግብሬ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እና ለሰላማዊ አገልግሎቶች የታለመ ነው ስትል ትሟገታለች፡፡
በቻይና የዓለማችን ልዕለ ፈጣን ባቡር ሙከራው እየተከናወነ መሆኑ ተሰማ፡፡
እጅግ ፈጣን ነው የተባለው አዲስ ስርቱ የቻይና ባቡር በሰዓት እስከ 453 ኪሎ ሜትር እንደሚምዘገዘግ ግሎባል ታይምስን የጠቀሰው አናዶሉ ፅፏል፡፡
አዲስ ስሪቱ ባቡር CR 450 ተሰንቷል፡፡፡
የዚህ ቀዳሚ CR 400 በሰዓት እስከ 350 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት እንደሚወነጨፍ መረጃው አስታውሷል፡፡
CR 450 ወደ ሙሉ አገልግሎት ከመግባቱ አስቀድሞ የ600 ሺህ ኪሎ ሜትር ሙከራ ማጠናቀቅ ይኖርበታል ተብሏል፡፡
አዲስ ስሪቱ ባቡር አገልግሎት ሲጀመር በሰዓት 400 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት እንዲሰራ መታሰቡ ታውቋል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments