top of page

ጥር 17፣ 2015- የጅቡቲ ወደብ መንገድ መጎዳት ስራዬን እያከበደብኝ ነው ሲል የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ተናገረ


ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የጭነት ምልልስ የምታደርግበት የጅቡቲ ወደብ መንገድ መጎዳት ስራዬን እያከበደብኝ ነው ሲል የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ተናገረ፡፡


የጋላፊ መንገድ በመጎዳቱ የጭነት አገልግሎትን ለማጓጓዝ እንዳማራጭ ደወሌን እየተጠቀምኩ ብሏል ድርጅቱ፡፡


ባለፉት 6 ወራት ከሰራው ስራ ከ2.1 ቢሊየን ብር በላይ ያልተጣራ ገቢን መግኘቱንም ተናግሯል፡፡


እኛ ይሄንን የሰማነው ተቋሙ የስራ አፈፃፀሙን በተመለከተ ዛሬ በዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሮባ መገርሳ በኩል ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጥ ተገኝተን ነው፡፡


ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሮባ እንዳሉት ያለፉት 6 ወራት የባህር ትራንስፖርት አገልግሎቱ በብዙ ምክንያቶች በፈተና ውስጥ አልፏል፡፡


የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በዚሁ ፈተና ውስጥ ቢያልፍም በስራው ግን ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል ብሏል፡፡


ከኮቪድ በኋላ በተለይም የምግብ ሸቀጥ 50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የዩክሬይን እና የሩሲያ ጦርነት የመርከቦችን ዝውውር እንዲቀየር ማድረጉና ሌሎችም የዘርፉ ፈተናዎች ነበሩ ብሏል፡፡


በአገር ውስጥም በውጪ ምንዛሬ እጥረት በተወሰኑ የገቢ ምርቶች ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት አጠቃላይ የገቢ ምርቱ ቀንሷል ብለዋል፡፡


ኢትዮጵያ ትልቁን የገቢና ወጪ ጭነትን የምታስተናግደው በጅቡቲ ወደብ በኩል መሆኑን ያነሱት ሀላፊው ወደ 3.5 ሚሊየን ቶን የኮንቴነር እና ብትን ገቢ ጭነት እንዲሁም ወደ 450,000 ቶን ወጪ ጭነት በጅቡቲ በኩል መስተናገዱን አንስተዋል፡፡


በወደብ አገልግሎቱ የጅቡቲ ወደብ ተመራጭ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ሮባ ወደ 60 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የጋላፊ መንገድ መበላሸቱ እና በታሰበው ፍጥነት አለመሰራቱ የጭነት ምልልሱን ፈተና ውስጥ ጥሎታል ብሏል፡፡


ለጊዜው በጋላፊ ምትክ የደወሌን መንገድ እየተጠቀምን ነው ያሉት ሀላፊው መንገዱ በፍጥነት ካልተገነባ ግን ችግሩ እየከፋ ይሄዳል ብለዋል፡፡


ባለፉት 6 ወራት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከሰራው ስራ ከ2.1 ቢሊየን ብር በላይ ያልተጣራ ገቢን ማግኘቱንም አንስተዋል፡፡


በወደቦች የነበረ የእቃ ቆይታ ጊዜን በማሳጠር የመርከቦችን የወደብ ቆይታ ወይንም የእፎይታ ጊዜን ዝቅ በማድረግና በሌሎችም መለኪያዎች ተቋሙ የተሳካ ጊዜን አሳልፌአለሁ ብሏል፡፡


ቴዎድሮስ ወርቁ


ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

https://bit.ly/33KMCqz

bottom of page