የኒውክሊየር ኃይል ከውሃ፣ ከንፋስና ከፅሐይ የኃይል አማራጮች በተሻለ ለኢትዮጵያ ምን የተለየ ነገር ይዞላት ይመጣ ይሆን?
- sheger1021fm
- 6 minutes ago
- 2 min read
ጥር 6/2018
ኢትዮጵያ 13 ቢሊየን ዶላር በጀት ይጠይቃል የተባለን የኒውክሊየር ሀይል ማመንጫ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነች፡፡
በውሃ፣ ነፋስና ፀሐይ ላይ ጥገኛ የነበረው የኤሌክትሪክ ሀይል አማራጭ የኒውክሊየር ሀይልንም ይጠቀማል ተብሏል፡፡
የኒውክሊየር ሀይል ግንባታ ለኢትዮጵያ ምን ይዞላት ይመጣል?
የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮምሽን ምክትል ኮሚሽነር ኢንጅነር አብዱልቃድር ዑመር የኒውክሊየር ኃይል ከሌሎች የአሌክትሪክ ኃይል አማራጮች በተሻለ በተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ እና ሌሎች ተፅዕኖ ውስጥ ሆኖ እንኳን የማይወዥቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ይችላል ይላሉ፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ ውሃ፣ ፀሐይ እና ንፋስ የኃይል አማራጮች የማመንጨት አስተማማኝነታቸው 50 ከመቶ በታች ሲሆን የኒውክለር ግን 92 በመቶ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ይህም ኒውክለርን ከሌሎች የኃይል አማራጮች የተሻለ እንደሚደርገው ነግረውናል፡፡
ኢንጅነር አሸብር ተስፋዬ ከሩስያው ባውማን ስቴት ቴክኒካል ዩንቨርሲቲ በኒውክለር ፓውር የማስተርስ ድግሪ አላቸው፡፡
እሳቸው ደግሞ ኒውክለር ከሌሎች የኃይል አማራጮች በተሻለ አንድ ሃገር የሚያስፈልጋትን የዝቅተኛ ወለል የኤሌክትሪክ ጭነት (minimum load) ሳያባክን ለረጅም ጊዜ ተሸክሞ የመቆየት አቅም እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

ባለሙያው ኢትዮጵያ ከአስር እና አስራ አምስት አመት በኋላ አሁን ካለው የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሁለት እና ሶስት እጥፍ የአሌክትሪክ ፍጆታ ያስፈልጋታል ያሉ ሲሆን የኒውክለር ኃይልን እንደ አማራጭ ካልተጠቀመች ይህንን የኃይል ፍላጎት በምንም ልትሸፍነው አትችልም ብለዋል፡፡
ኢንጂነር አሸብር ከነዳጅ ተላቃ ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ የኃይል አማራጭ ለመግባት ዕቅድ የያዘች ሀገር የማይቆራረጥና የኢነርጂ ሉዓላዊ ደህንነትን የሚጠብቅ የኃይል ምንጭ ያስፈልጋታል፣ ለዚህም የኒውክለር ኃይል ተመራጭ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ባለሙያው የኒውክለር ኃይል የተሻለ የኃይል አማራጭ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የኒውክለር ኃይልን በመገንባት ሂደት ውስጥ ብዙ የሚያገጥሟት ፈተናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡
ከፈተናዎቹም መካከል በዋናነት በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል እጥረትና የኒውክለር ኃይል ግንባታ ፕሮጅክት ማስኬጃ በጀት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ መክረዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ንጋት መኮንን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…..
YouTube : https://url-shortener.me/2DTR
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://url-shortener.me/2DTY
WhatsApp :https://url-shortener.me/2DU0
Website፡ https://www.shegerfm.com/
LinkedIn :https://url-shortener.me/2DU8
Tiktok : https://url-shortener.me/2DUB
Instagram : https://url-shortener.me/2DUD












Comments