top of page

ጥር 13፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


በአሜሪካ የፍሎሪዳው አስተዳዳሪ ሮን ዲሳንቲስ ሪፖብሊካዊውን የፖለቲካ ማህበር በመወከል በፕሬዘዳንታዊ እጩነት ለመቅረብ ከሚደረገው ፉክክር ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናገሩ፡፡


ዲ ሳንቲስ ራሳቸውን ከፉክክሩ ያገለሉት የኒው ሐምሻየር ሪፖብሊካውያን ድምፅ ሰጭዎች ለእጩዎቹ ምርጫ ድምፅ ከመስጠታቸው አስቀድሞ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የፍሎሪዳ አስተዳዳሪ በእጩነት ለመቅረብ ከሚዳረገው ፉክክር ወጥቻለሁ ያሉት በምርጫ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሻለ እድል ስላላቸው ነው ብለዋል፡፡


ዲሳንቲስ ከቀድሞው ፕሬዘዳንት ጋር በብዙ ጉዳዮች ልዩነት ቢኖራቸውም በዋናው ምርጫ ዴሞክራቱን ፕሬዘዳንት ጆ ባይደንን ለመርታት ትራምፕ ሁነኛው ሰው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡


ሪፖብሊካዊውን የፖለቲካ ማህበር ወክሎ በእጩነት የሚቀርብ ፖለቲከኛ በስልጣን ላይ ከሚገኙት ጆ ባይደን ጋር በመጪው አመት በሚዳረግ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እንደሚፎካከር ዘገባው አስታውሷል፡፡




በቻይና ደቡባዊ ምዕራብ ዩናን ግዛት በደረሰ የመሬት መንሸራተት 50 ያህል ሰዎች በማጥ ውስጥ መቀበራቸው ተሰማ፡፡


አደጋው ካጋጠመበት ስፍራ ሌሎች ሰዎች ከአደጋ ወደሚጠበቁበት ስፍራ እንዲዛወሩ መደረጉን ABC ፅፏል፡፡


ፕሬዘዳንት ሺ ጂን ፒንግ በማጥ ውስጥ የተቀበሩትን ሰዎች ለማትረፍ የነፍስ አድን ጥረት እንዲፋጠን ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡


በመሬት መንሸራተቱ ህንፃዎች እና ቤቶች መፍረሳቸው ታውቋል፡፡


የነፍስ አድን ጥረቱ የሚከናወነው በፍርስራሽ ስርም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


በቻይና ዩናን ግዛት የመሬት መንሸራተት እንደሚደጋገም ዘገባው አስታውሷል፡፡



በሩሲያ እጅ በሚገኘው የምስራቃዊ ዩክሬይን ዳኔስክ ከተማ አቅራቢያ በተፈፀመ የመድፍ ድብደባ በጥቂቱ 25 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡


ድብደባው የተፈፀመው በገበያ ስፍራ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡


በድብደባው ከሞቱት ሌላ ከ20 የማያንሱት ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ፍራንስ 24 ፅፏል፡፡


ድብደባውን በተመለከተ ከኪየቭ ሹሞች በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡


ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሩሲያ እና ዩክሬይን ግዛት ተሻጋሪ የከባድ መሳሪያ እና የድሮን ጥቃት እየፈፀሙ ነው፡፡

ጦርነቱ ወደ 2ኛ አመቱ እየተቃረበ ነው፡፡



በኮሞሮስ አዛሊ ኣሱማኒ ለ5ኛ ጊዜ አሸንፈውበታል የተባለው የፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ውጤት እንዲሰረዝ ዋነኛው የተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር ለፍርድ ቤት አቤት አለ፡፡


ኣሱማኒ በምርጫው ለ5ኛ የ5 አመት ጊዜ ማሸነፋቸው የታወጀው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡


ተቃዋሚዎች ግን ምርጫው ነፃ ፣ ፍትሃዊ እና ግልፅ አልነበረም በሚል እየተቃወሙ ነው፡፡


አሳፋሪም ሲሉ ጠርተውታል፡፡


ባለፈው ሳምንት ውጤቱን በመንቀፍ በርዕሰ ከተማዋ ሞሮኒ ሰልፍ የወጡ የተቃዋሚዎቹ ደጋፊዎች ከፀጥታ ሀይሎች ጋር እስከመጋጨት ደርሰዋል፡፡


በአገሪቱም ከምሽት እስከ ንጋት የሚዘልቅ የሰዓት እላፊ ስራ ላይ ከዋለ መሰንበቱን አናዶሉ አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




bottom of page