top of page

ግንቦት 27 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Jun 4
  • 2 min read

ሱዳን ውስጥ የተባበሩት መንግስታትን የእርዳታ ምግብ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት አምስት የረድኤት ሰራተኞች ተገደሉ፡፡


በጥቃቱ አካላዊ ጉዳት የገጠማቸው እንዳሉ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


እርዳታ በጫኑት ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የደረሰባቸው የሰሜናዊ ዳርፉር ማዕከል ወደሆነችው ኤል ፋሸር ከተማ በማመራት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

ree

ከተማይቱ በRSF ተከባ መቆየቷ ይነገራል፡፡


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥቃቱን በብርቱ አውግዞታል፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በዚሁ ጥቃት አድራሽነት በአንተ ነህ ፤ አንተ ነህ እየተካሰሱ ነው ተብሏል፡፡

ድርጅቱ ግን ጥቃቱ በዝርዝር እንዲጣራ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡



የዩክሬይን የደህንነት ሹሞች ከሩሲያ ወደ ክራይሚያ ልሳነ ምድር የተዘረጋውን ድልድይ መትተን ጉዳት አድርሰንበታል አሉ፡፡


የዩክሬይን የደህንነት ሹሞች የኮርችን ድልድይ በውሃ ላይ በሚሳፈፉ ድሮኖች መትተን ጉዳት አድርሰንበታል ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ድልድዩ ከዚህ ቀደምም የዩክሬይን የጥቃት ዒላማ እንደነበር ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡


ከሩሲያ ወገን በድልድዩ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ አልተካደም፡፡


ሆኖም የሩሲያ ሹሞች ድልድዩ አገልግሎት ለማቋረጥ የሚያስገድድ ጉዳት አልደረሰበትም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ዩክሬይን ሰሞኑን በሩሲያ የአየር ሀይል ሰፈሮች ላይ ባደረሰችው የተቀነባበረ የድሮን ጥቃት 40 ስትራተጂያዊ ቦምብ ጣይ አውሮፕላችን ማውደሟ ሲነገር ሰንብቷል፡፡


የሁለቱ አገሮች ወሰን ተሻጋሪ ጥቃት እየተጠናከረ ነው ተብሏል፡፡



የብሪታንያ መንግስት ለእስራኤል የጦር መሳሪያ እንዳይሸጥ እና እንዳያቀብል ከፓርላማው እንደራሴዎች ግፊት በርትቶበታል ተባለ፡፡


ራሱን ገዢውን የሌበር የፖለቲካ ማህበር ወክለው በፓርላማው የሚገኙ አባላት ጭምር የጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር ስታርመር መንግስት ለእስራኤል የጦር መሳሪያ እንዳይሸጥላት እንዲያደርግ እየጎተጎቱ መሆኑን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ለእስራኤል 30 ዓይነት የጦር መሳሪያዎች እንዳይሸጡ የሚከለክል የፈቃድ ስረዛ አድርገዋል ተብሏል፡፡


ያም ሆኖ ብሪታንያ አሁንም 100 ዓይነት የጦር መሳሪያዎችን ለእስራኤል በማቅረብ ላይ መሆኗ ተጠቅሷል፡፡


አሁን እንደራሴዎቹ መንግስት ከነአካቴው ወደ እስራኤል ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ እንዳይልክ እየጎተጎቱ ነው ተብሏል፡፡


የእስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻ በአሁኑ ወቅት መጠነ ሰፊ ነቀፋ እና ተቃውሞ እያስከተለባት መሆኑ ይነገራል፡፡



በፓኪስታን በርዕደ መሬት ቱማታ ከ200 በላይ እስረኞች እስር ቤት ሰብረው ማምለጣቸው ተሰማ፡፡


የእስረኞች ማምለጡ የተከሰተው በካራቺ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡


በአካባቢው ደርሶ ነበር የተባለ ርዕደ መሬት የፈጠረው ግርግር ለእስረኞቹ ማምለጥ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡


እስረኞቹ በመሬት ነውጡ ወቅት ለደህንነታቸው ከእስር ክፍሎቻቸው እንዲወጡ ተደርገው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡


እስረኞቹ አጋጣሚውን ከዚያ ለማምለጥ እንደተጠቀሙበት ታውቋል፡፡


በፓኪስታን የእስር ቤት ሰበራ እምብዛም አይፈፀምም ይባላል፡፡


የአሁኑ በአገሪቱ ታሪክ ታላቅ ከእስር ቤት የማምለጥ አጋጣሚ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


ፖሊስ 80 ያህሉን አምላጮች መልሼ ይዣቸዋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page