በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶች ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል ተባለ።
- 1 hour ago
- 1 min read
ሰኔ 5/2018
በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶች ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው የማስፋፊያ እና ለአዲስ ኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል ተባለ።
በግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ ለማስፋፊያ እና ለአዲስ ኢንቨስትመንት የሚውል ተጨማሪ 33,000 ሄክታር መሬት በተለያዩ ክልሎች መገኘቱ ተነግሯል፡፡
እስከ አሁን ልማቱ ሲካሄድ የቆየው በ12,000 ሄክታር መሬት እንደነበር ከኢትዮጵያ አበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ሠምተናል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ 120 የሚሆኑ ባለሃብቶች በአበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው እንደሚገኙ ተነግሯል።
እነዚህ ባለሃብቶች እየሰሩ ያሉት 12,000 ሄክታር መሬት ላይ እንደሆነ ከኢትዮጵያ አበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች እና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ሠምተናል።

ከዚህ ውስጥ 1,750 ሄክታር መሬቱ አበባ አልሚዎች የሚጠቀሙበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ባለሃብቶቹ ለማስፋፊያ እና ለአዲስ ኢንቨስትመንት የሚውል ተጨማሪ መሬት እንዲሰጣቸው በማህበራቸው በኩል ለተደጋጋሚ ጊዜ ሲያቀርቡ እንደቆዩም አቶ ቴዎድሮስ አስታውሰዋል።
በግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ ጭምር ጥያቄው አሁን ምላሽ አግኝቷል ብለዋል።
ኦሮሚያ ፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፤ ደቡብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ለዘርፉ ልማት የሚሆን ተጨማሪ መሬት ማቅረባቸውን ነው የነገሩን።
ክልሎቹ በአጠቃላይ 33 ሺህ ሄክታር መሬት ለአዲስ ኢንቨስትመንት እና ለማስፋፊያ የሚውል መሬት አቅርበዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ ኢትዮጵያውን በዘርፉ የተሻለ ተፎካካሪ የሚያደርጋት ውሳኔ እንደሆነ አክለዋል።
ውሳኔ አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሰማሩ ዕድል የሚከፍት ነውም ተብሏል፡፡
በስራ ላይ ያሉና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ላለፉት አምስት ዓመታት ምንም አይነት ማስፋፊያ ሳያደርጉ መቆየታቸውን አቶ ቴዎድሮስ ጨምረው ነግረውናል።
በኢትዮጵያ የአበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት አሁን ካለው በአስር እጥፍ ማደግ እንደሚችልም ጠቅሰዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…..
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/





Comments