ግንቦት 25 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- 2 days ago
- 1 min read
አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ካሚል ኢድሪስ ቃለ መሐላ በመፈፀም ሀላፊነታቸውን ተረከቡ፡፡
ካሚል ኢድሪስ የቃለ መሐላ ስነ ስርዓትን ያከናወኑት የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት የተሰኘው አካል የበላይ የሆኑት ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በተገኙበት እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
በዚህም ካሚል ኢድሪስ ከትናንት በስቲያ አንስቶ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡

አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ነባር ዲፕሎማት እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡
በአለም አቀፍ ህግም የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡
ካሚል ኢድሪስ በአገሪቱ ወታደራዊ መሪ ጄኔራል ቡርሃን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ከ10 ቀናት በፊት ነበር፡፡
ከካሚል ኢድሪስ በፊት ዳፋላ አል ሐጅ ዩሴፍ ባለ አደራ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡
በአሜሪካ ኮሎራዶ በሚገኝ የገበያ ማዕከል አንድ ግለሰብ በሰዎች ላይ በፈፀመው እሳት የመልቀቅ ጥቃት ስድስት ሰዎች አካላዊ ጉዳት ገጠማቸው ተባለ፡፡
ግለሰቡ በገበያ ስፍራው በነበሩ ሰዎች ላይ ሞሎቶቭ ኮክቴል የተሰኘውን ጓዳ ሰራሽ ተቀጣጣይ ቁስ በመወርወር በስድስቱ ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረሱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ስፍራው በሐማስ ተይዘው የሚገኙ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ሰዎች መሰባሰቢያ ነበር ተብሏል፡፡
ግለሰቡ ተቀጣጣይ ቁሱን በሚወረውርበት ወቅት ነፃነት ለፍልስጤም ብሎ ይጮህ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
የአሜሪካ ፌዴራል የምርመራ ቢሮ /FBI/ ሹሞች የግለሰቡ ድርጊት የሽብር ጥቃት እንደሆነ እንጠረጥራለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኮሎራዶውን ጥቃቱ የፀረ ሴማዊነት ውጤት ነው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
በናይጀርያ ካኖ ግዛት በደረሰ የአውቶብስ መገልበጥ አደጋ የ22 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ፡፡
አደጋ የገጠመው አውቶብስ 30 መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበር አልጀዚራ ፅፏል፡፡
አደጋው የደረሰው አውቶብሱ ከድልድይ ላይ በመውደቁ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በአውቶብሱ ላይ ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች ከስፖርታዊ ውድድሩ በመመለስ ላይ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡
አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸው ከመሞት የተረፉት ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተጠቅሷል፡፡
አደጋው በምን ምክንያት እንዳጋጠመ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም ተብሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
በአደጋው ምክንያት በካኖ ግዛት ለዛሬ ብሔራዊ ሐዘን መታወጁ ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentários