top of page

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ "ሁሉ ስፖርት" የኦንላይን ውርርድ ድርጅት ላይ ተላልፎ የነበረውን የንግድ ፈቃድ ስረዛ ውሳኔ በሙሉ ድምፅ ሻረ።

  • 4 hours ago
  • 2 min read

ሐምሌ 23 2018


የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ "ሁሉ ስፖርት" የኦንላይን ውርርድ ድርጅት ላይ ተላልፎ የነበረውን የንግድ ፈቃድ ስረዛ ውሳኔ በሙሉ ድምፅ ሻረ።



ሆኖም የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በውሳኔው ላይ ይግባኝ ማቅረቡን ተከትሎ፣ ከ14/11/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚቆይ ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።


የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ከህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የ22 የስፖርት ውርርድ ድርጅቶችን የሥራ ፈቃድ ማገዱ ይታወሳል።

ፈቃዱ ከተሰረዘባቸው ድርጅቶች አንዱ የሆነው "ሁሉ ስፖርት"፣ ውሳኔው የመሰማት መብቱን የጣሰና ሕገ-ወጥ ነው በማለት በሎተሪ አገልግሎቱና በገቢዎች ሚኒስቴር ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ነበር።


የተጠቀሱት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በበኩላቸው ድርጅቶቹ በከፍተኛ የግብር ስወራ፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና መመሪያን በተጣሰ የውርርድ አሠራር ላይ በመሰማራታቸው ፈቃዳቸው በቋሚነት እንዲሰረዝ መወሰኑን የተገባ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።


እንዲሁም ድርጅቶቹ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር በማሳጣታቸውና አሠራራቸው በሀገር ደኅንነትና ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት በማድረሱ እርምጃው ተገቢ ነው ሲሉም ተከራክረዋል።


"ሁሉ ስፖርት" በበኩሉ ውሳኔው የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅን የጣሰና ጥፋቱ ሳይነገረው እንዲሁም የመከላከያ ማስረጃ ሳያቀርብ የተወሰነብኝ ነው ሲል አቤቱታ አቅርቧል።


ድርጅቱ አክሎም ከፍተኛ ግብር ሲከፍልና በርካታ የሥራ ዕድል ሲፈጥር የቆየ በመሆኑ፣ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ "ጥፋተኛ" ተብሎ ፈቃዱ መሰረዙ ሕገ-መንግሥታዊ መብትን ያልጠበቀ እንደሆነ ተናግሯል።


የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲያስተላልፉ በአዋጅ ቁጥር 1183/2012 የተደነገጉትን መርሆዎች የመከተል ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሷል።


ፍርድ ቤቱ የግብር ስወራና የሕገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ክሶች በወንጀል ሕግ የሚታዩና በማስረጃ ሊረጋገጡ የሚገባቸው እንጂ፣ በደፈናው ለፈቃድ ስረዛ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ብሏል።


ተቋማቱ የድርጅቱን ፈቃድ ከመሰረዛቸው በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ አለመስጠታቸውና ምላሽ የመስጠት ዕድል አለመፍቀዳቸው ጥፋት መሆኑንም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ አስፍሯል።


በዚህ መሠረት ፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግን ባለመከተልና የመሰማት መብትን በመጣስ የተተላለፈውን የንግድ ፈቃድ ስረዛ ውሳኔ መሻሩን ከሰጠው ውሳኔ ተመልክተናል።


ጥፋት መፈጸሙ በተጨባጭ ሲረጋገጥ እርምጃ መውሰድ ቢቻልም፣ በሁሉም የስፖርት ውርርድ ድርጅቶች ላይ በጅምላ ውሳኔ ማሳለፍ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ጠቅሷል።


ስለሆነም ተከሳሾች እርምጃ መውሰድ ከፈለጉ ሕግን የተከተለ ሥነ-ሥርዓት እንዲከተሉና የድርጅቱን የመከራከር መብት እንዲያከብሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።


ውሳኔውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ፣ የውሳኔው አፈጻጸም ካለፈው ሐምሌ 14 ቀን ጀምሮ ለ15 ቀናት እንዲታገድ ተደርጓል።


በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶት አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም የስፖርት ውርርድ (Sport Betting) ድርጅት እንደሌለ ጠቅሶ ዜጎች ህገወጥ ውርርድ ከማካሄድ እንዲታቀቡ ያሳሰበበትን መግለጫ ከፍርድ ሂደቱ ውሳኔ በኋላ በማህበራዊ በትስስር ገፁ አስነብቧል።


ገዛ ጌታሁን




Recent Posts

See All
የሐምሌ 23 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ግብፅ በግብፅ የሜዴትራኒያን የባህር ዳርቻ የነበረ የአሜሪካ የጋዝ ማጠራቀሚያ መርከብ በድሮን ተመታ ተባለ፡፡ ሁለት የደህንነት ምንጮች መርከቡ በድሮን እንደተመታ አረጋግጠውልኛል ሲል ሬውተርስ ፅፏል፡፡ መርከቡ በድሮን እንደተመታ በእሳት መያያዙ ታውቋል፡፡ ቃጠሎው ወደ ሌላ መርከብም ተጋብቶ ነበር ተብሏል፡፡ ኋላ ግን

 
 
 
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግ፣አፍሪካዊያን የጋራ መጪ እድላቸውን እንዲቀርፁ ማገዝ ያስፈልጋል ተባለ።

ሐምሌ 23 2018 የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግ፣አፍሪካዊያን የጋራ መጪ እድላቸውን እንዲቀርፁ ማገዝ ያስፈልጋል ተባለ። የአፍሪካ ሀገሮች እርስ በእርስ፣በአፍሪካና በሩሲያ እንዲሁም አፍሪካ ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳደግን ዓለማው ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተባበሩት መንግስታት የአ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page