top of page

ግንቦት 18 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • May 26
  • 2 min read

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ ህብረት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ ያሰቡትን የቀረጥ ታሪፍ ጭማሪ በ1 ወር አራዘሙት፡፡


ትራምፕ በህብረቱ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ የ50 በመቶ የቀረጥ ታሪፍ ለመጣል ተሰናድተው እንደነበር ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ree

ቀደም ሲል ትራምፕ ሕብረቱ መሰረታዊ የተባለውን የ10 በመቶ የቀረጥ ታሪፍ ይከፍላል ብለው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል የንግድ እና ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት ንግግር እየተካሄደ ነው፡፡


ትራምፕ አዲሱን የ50 በመቶ የቀረጥ ታሪፍ እርምጃቸውን በተጨማሪ 1 ወር ያራዘሙት ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዘዳንቷ ኡርሱላ ቮን ዴር ሊየር ጋር በስልክ ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት የቀረጥ ታሪፍ ቁለላ ህብረቱን ከአሜሪካ ጋር ክፉ ደግ ሲያነጋገር መሰንበቱን መረጃው አስታውሷል፡፡



የዩጋንዳ ጦር ከጀርመን ጋር የነበረኝን ማንኛውም ወታደራዊ ትብብር አቋርጫለሁ አለ፡፡


የዩጋንዳ ጦር ከጀርመን ጋር የነበረውን ወታደራዊ ትብብር ያቋረጠው በአገሪቱ የሚገኙ የአውሮፓዊቱ አገር አምባሳደር በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገቡ በማስቸገራቸው የተነሳ ነው ማለቱን ዴይሊ ሞኒተር ፅፏል፡፡


አምባሳደሩ ስርዓት ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ጋር እየተባበሩ ነው ሲልም የጀርመኑን አምባሳደር ከስሷቸዋል፡፡


እርምጃው በሁለቱ አገሮች መካከል ከባድ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ መቀስቀሱ እንደማይቀር ተገምቷል፡፡


ወታደራዊ ትብብር ማቋረጡ ወዲያውኑ ስራ ላይ የሚውል ነው ተብሏል፡፡


በዚህ ጉዳይ ከዩጋንዳ የጀርመን አምባሳደርም ሆነ ከአውፓዊቱ አገር የተሰጠ ፈጣን ምላሽ በመረጃው አልተጠቀሰም፡፡



የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ መደፍረስ በእጅጉ አሳስቦናል አለ፡፡


በዋነኞቹ ተቀናቃኞች በሱዳን መንግስት ጦር እና SPLM-IO በተሰኘው የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች እየተደጋገሙ መምጣታቸውን ጁሪስት ኒውስ ፅፏል፡፡


ደቡብ ሱዳን ካለፈው የካቲት ወር አንስቶ ወደ ሌላ ዙር ፖለቲካዊ ቀውስ ማምራቷ ሲነገር ቆይቷል፡፡


SPLM-IO የተሰኘው የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት መሪ እና የአገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ሪያክ ማቻር ከዚያን ጊዜ አንስቶ በቁም እስር እንደዋሉ ነው፡፡


55 ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ አባሎችም ታስረዋል ተብሏል፡፡


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለውጥረቱ መርገብ እስረኞቹ እንዲለቀቁ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡


በደቡብ ሱዳን ከ8 አመታት በፊት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለመክሸፍ በቋፍ ላይ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡



በሱዳን ካርቱም ግዛት የኮሌራ መከላከያ ክባት እየተሰጠ ነው፡፡


በግዛቲቱ ላለፉት 4 ሳምንታት የኮሌራ ወረርሽኝ ሲዛመት መቆየቱን ሬዲዮ ዳባንጋ ፅፏል፡፡


በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኮሌራ ተይዘዋል ተብሏል፡፡


ባለፈው ሳምንት አርብ ብቻ በበሽታው የ24 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡


በካርቱም እና በመንትየዋ ኦምዱርማን አዳዲስ የኮሌራ ሕሙማን ማስተናገጃ ማእከሎች መከፈታቸው ታውቋል፡፡


ሱዳን ከ2 አመታት በላይ በጦርነት ላይ መሆኗን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page