የካቲት 2/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 8 minutes ago
- 1 min read
የካቲት 2/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
በጃፓን LDP መራሽ ገዢ የፖለቲካ ጥምረት አብዛኛውን የፓርላማ መቀመጫ አሸነፈ ተባለ፡፡
ጥምረቱ 465 መቀመጫዎች ባሉት የህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት 352ቱን ማሸነፉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡

LDP ብቻውን 316 መቀመጫዎችን ማሸነፉ እንደ ታላቅ የምርጫ ስኬቱ ተቆጥሮለታል፡፡
ይሄ የፓርላማ አብላጫነት ለአዲሲቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካይቺ ከፍተኛ አቅም ይፈጥርላቸዋል ተብሏል፡፡
ታካይቺ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡
ከሳቸው ቀዳሚ የነበሩ ሁለት የLDP ጠቅላይ ሚኒስትሮች የፓርላማውን አብላጫነት አጥተው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
የሶማሊያ የፀጥታ ሀይሎች 8 የአልሸባብ ፅንፈኛ ቡድን ታጣቂዎችን ገደልን አሉ፡፡
8ቱ የአልሸባብ ታጣቂዎች የተገደሉት በመካከለኛ ጁባ ግዛት ቡአሌ በተባለው ከተማ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ጦር በዚሁ ዘመቻው ፅንፈኛው ቡድን እንደ ዋና ፅህፈት ቤቱ የሚገለገልበትን ስፍራ ምንቅርቅሩን አውጥቼዋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በጦር ተባባሪዎቹ የሚደገፈው የሶማሊያ መንግስት ጦር ከፅንፈኛው ቡድን ጋር ሲዋጋ ከ16 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡
ጦሩ ከቅርብ አመታት ወዲህ በፅንፈኛው ቡድን ላይ ተከታታይ ዘመቻዎችን እያካሄደ መሆኑ ይነገራል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ የተሰማራውን አፍሪካዊ ሀይል ተልዕኮ በአመት እንዳራዘመው መረጃው አስታውሷል፡፡
ደቡብ አፍሪካ በኮንጎ ኪንሻሣ ከተሰማራ በቆየው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሀይል ወታደሮቿን ልታስወጣ ነው፡፡
የደቡብ አፍሪካ ሰላም አስከባሪዎች ከኮንጎ ኪንሻሣ ለቅቀው የሚወጡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ለማቃለል በተደረሰ መግባባት እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ሙንስኮ በሚል ምህፃር የሚጠራው ሰላም አስከባሪው በኮንጎ ኪንሻሣ ከተሰማራ 17 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ያም ሆኖ አሁንም ድረስ በኮንጎ ኪንሻሣ ምስራቃዊ ክፍል በጭራሽ ሰላም የለም፡፡
የAFC የአማፂያን ጥምረት ከመንግስት ጦር ጋር እየተዋጋ ነው፡፡
M 23 የተሰኘው አማጺ ቡድንም የዚሁ ጥምረት አካል መሆኑ ይነገራል፡፡
አማጺያኑ በጎረቤት ሩዋንዳ እንደሚደገፉ ይነገራል፡፡
ሩዋንዳ ግን በዚህ ረገድ የሚቀርብባትን ውንጀላ በተደጋጋሚ ታስተባብላለች፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7








