top of page

የነሐሴ 22፣2015 የባህር ማዶ ወሬዎች



የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ሰሞኑን የአሜሪካው አምባሳደር የሰነዘሩትን እና አሉታዊ ነው ያለውን አስተያየት እንዲያርሙለት ጠየቃቸው፡፡


በሱዳን የአሜሪካው አምባሳደር ጆን ጎድፍሬይ ሰሞኑን በሰነዘሩት አስተያየት አገር የመምራት ብቃት የላቸውም ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF የተሰኘው ፍጥኖ ደራሽ ሀይል ጦርነት ከገጠሙ ከ4 ወራት በላይ ሆኗቸዋል፡፡


የአሜሪካው አምባሳደር ተፋላሚዎቹ በአፋጣኝ ጦርነቱን ማቆም ይገባቸዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የሱዳን ወታደራዊ መንግስት የአሜሪካው አምባሳደር ከተፋላሚዎቹ አንዳቸውም አገር የመምራት ብቃት የላቸውም ማለታቸው አስቆጥቶታል፡፡


በዚህ ጉዳይ ከፈጥኖ ደራሹ ሀይል በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም ተብሏል፡፡



የሩሲያ የአደጋ መርማሪዎች የስልጡን ቅጥር ወታደሮች /የዋግነር/ ኩባንያ የበላይ የነበሩት ይቭጌኒ ፕሪጎዚን በአውሮፕላን አደጋ መሞታቸውን አረጋግጠናል አሉ፡፡


ፕሪጎዚንን እና ሌሎች 9 ሰዎችን ያሳፈረ አውሮፕላን ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ በማምራት ላይ ሳለ የተከሰከሰው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡


ከአደጋው በሕይወት የተረፈ የለም፡፡


የአደጋ መርማሪዎች በባህሪ ወሳኝ ቅንጣት /DNA/ ምርመራ ፕሪጎዚን መሞታቸውን አረጋግጠናል እንዳሉ ፎክስ ኒውስ ፅፏል፡፡


የአውሮፕላኑ አደጋ አነጋጋሪነቱ አልሰከነም፡፡


ፕሪጎዚን ተሳፍረውበት የነበረው አውሮፕላን በሚሳየል ተመትቷል ቢባልም የክሬምሊን ሹሞች አስተባብለዋል፡፡


የዋግነር እጣ ፈንታም አልለየለትም፡፡



የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የፍልስጤማውያኑን የጦር እና የፖለቲካ ድርጀት /ሐማስ/ መሪዎችን በብርቱ ማስጠንቀቃቸው ተሰማ፡፡


ኔታንያሁ የሐማስ መሪዎችን ያስጠነቀቁት በዌስት ባንክ አመፅ እንቀጣጠል እየቀሰቀሱ ነው በሚል እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የሐማስ መሪዎች ከቅስቀሳቸው ካልታቀቡ የእጃቸው ያገኛሉ ሲሉ ዝተዋል፡፡


ዌስት ባንክ የፍልስጤማውን ይዞታ ቢሆንም በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በዚያ ይኖራሉ፡፡


በዌስት ባንክ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግጭት እየተደጋገመ መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

bottom of page