የሩሲያ የውጭ የስለላ ተቋማት SVR የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የማይፈልጓቸውን የአፍሪካ መሪዎችን የማስገደል ሙከራ አድርገዋል ሲል ከሰሰ፡፡
- sheger1021fm
- 42 minutes ago
- 2 min read
ጥር 26/2018 – የውጪ ሀገራት ወሬዎች
# ሩሲያ
የሩሲያ የውጭ የስለላ ተቋማት SVR የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የማይፈልጓቸውን የአፍሪካ መሪዎችን የማስገደል ሙከራ አድርገዋል ሲል ከሰሰ፡፡
SVR ማክሮን ዘመናዊውን የእጅ አዙር ቅን አገዛዝ አሻፈረን ያሏቸውን እና በራሳቸው ለመቆም እየጣሩ ያሉ አገሮችን መሪዎች ለማስገደል ትዕዛዝ ሰጥተዋል ማለቱን አናዶሉ ጽፏል፡፡
ከወር በፊት በቡርኪናፋሶ ተደርጎ ነበር ያለውን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ በምሳሌነት አንስቷል የውጭ የስለላ ድርጅቱ፡፡
ውስጥኑ በፀረ ቅኝ አገዛዝ አቋማቸው የሚታወቁትን የቡርኪናፋሶው መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬን ለማስገደል ጭምር የተዶለተ ነበር ማለቱ ተጠቅሷል፡፡
ቡርኪናፋሶ ፣ ማሊ እና ኒጀር የፈረንሳይ የጦር ትብብር አያሻንም ያሉ አገሮች ናቸው፡፡
የፈረንሳይን ወታደሮችም ከየአገሮቻቸው አስወጥተዋል፡፡
ፈረንሳይ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፖብሊኩን መሪም ለማስገደል እያሴረች ነው ብሏል SVR ፡፡
ፈረንሳይ በዚህ ጉዳይ የሰጠችው ምላሽ በዘገባው አልተጠቀሰም፡፡
ጋና በውጭው አለም ለሚኖሩ ትውልደ አፍሪካዊያን የምትሰጠውን ዜግነት በጊዜያዊነት አቋረጠች፡፡
ባለፉት 10 ዓመታት የቅድመ አያቶቻቸው የዘር ግንድ ከአፍሪካ እንደሆነ ላረጋገጡ በውጭው አለም ነዋሪ ትውልደ አፍሪካዎች ጋና ዜግነት ስትሰጥ መቆየቷን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
እስካሁንም በዚሁ መላ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች የጋናን ዜግነት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
የጋናን ዜግነት ካገኙት መካከል ታዋቂው የዘፈን ፀሐፊ አፍሪካ አሜሪካዊው ስቲቭ ዎንደር አንዱ ነው ተብሏል፡፡
ይሁንና የጋናው የዜግነት ማመልከቻ ድረ ገፅ አለበት በተባለ እንከን ምክንያት ለጊዜው የዜግነት ቅበላው ሒደት መቋረጡን ሹሞች ተናግረዋል፡፡
ጥያቄቸው ተቀባይነት የሚያገኝ ሰዎች ተዛማጅ ማስጃዎችን በ1 ሳምንት ጊዜ ማቅረብ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ለብዙዎቹ አስቸጋሪ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ዜግነት የማግኛው ሒደት እስከ 2,400 ዶላር ያህል ክፍያ እንደሚጠየቅበት መረጃው አስታውሷል፡፡
በናይጀርያ ሰሜናዊ ግዛት ከሳምንታት በፊት ከ3 ቤተ እምነቶች ታግተው ከነበሩት 177 ሰዎች መካከል 80ው ወደ ቀያቸው ተመለሱ ተባለ፡፡
80ዎቹ ታጋቾች በታገቱበት እለት ከአጋቾቻቸው ማምለጣቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ሆኖም ለአጋቾቻቸው እይታ ላለመጋለጥ ራሳቸውን ሸሽገው መሰንበታቸው ተሰምቷል፡፡
ቀሪዎቹ 86 ታጋቾች ግን አሁንም እንደተያዙ ነው ተብሏል፡፡
የፀጥታ ሹሞች ቀሪዎቹን ታጋቾች ለማስለቀቅ ጥረታቸው እንደሚያቋርጡ ተናግረዋል፡፡
በናይጀሪያ በአሁኑ ወቅት የሰላማዊ ሰዎች እገታ የወረርሽኝ ያህል መሆኑ ይነገራል፡፡
ፅንፈኛ ታጣቂዎች ከሚፈፅሙት እገታ በተጨማሪ የታጠቁ ሽፍቶች እና የተደራጁ ወንበዴዎች የማስለቀቂያ የቤዛ ክፍያ ጥየቃ እገታ እንደሚፈፅሙ መረጃው አስታውሷል፡፡
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዘዳንት ሳልቫ ኪር የግዛት አስተዳዳሪዎች ሹም ሽር አደረጉ፡፡
የምዕራባዊ ኢኳቶሪያል ግዛት አስተዳዳሪ እና የምዕራባዊ ባህር ኤል ጋዛል ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ ከሀላፊነት ተባረው በሌሎች ሹሞች መተካታቸው ታውቋል፡፡
የሹም ሽሩ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫ እወቁት ቢባልም ምክንያቱ ግን አልተጠቀሰም፡፡
ከሀላፊነት የተባረሩትም ሆነ አዲስ የተሾሙት የገዢው የSPLM አባሎች እንደሆኑ ሬዲዮ ታማዙጅ ፅፏል፡፡
የግዛት አስተዳዳሪዎቹ ሹም ሽር የተደረገው አገሪቱ ወደ አዲስ ቀውስ ባመራችበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ሪያክ ማቻር በመንግስት ላይ አመፅ አስነስተዋል ተብለው በአገር ክህደት ክስ በእስር ላይ እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ








