top of page

የሐምሌ 30 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

  • 2 days ago
  • 2 min read


ኢራን በአሜሪካ አዲስ ጥቃት የሚከፈትብኝ ከሆነ እኔም የባህረ ሰላጤውን የአሜሪካ ተባባሪዎች አልለቃቸውም ማለቷ ተሰማ፡፡


ቴሕራን በአሜሪካ ዳግም ጥቃት የሚሰነዘርብኝ ከሆነ እኔም የባህረ ሰላጤውን አገሮች የነዳጅ አውታሮች እንዳልነበሩ አድርጌ አወድማቸዋለሁ ማለቷን የፃፈው ሬውተርስ ነው፡፡


ስለዚህ ጉዳይ በስም መጠቀስ ያልፈለጉ የኢራን እና የባህረ ሰላጤው አገሮች ሹሞች ተናግረዋል ተብሏል፡፡


የኢራኑ ቀውስ የዲፕሎማሲያዊ ንግግር እና የጦር ዛቻ ፍርርቅ በዝቶበታል፡፡


ቀደም ሲል እንደ ካታር ፣ ኦማን እና ሳውዲ አረቢያ ያሉ የባህረ ሰላጤው አገሮች አሜረካ ዲፕሎማሲያዊ ንግግርን እንድታስቀድም ሲጎተጉቱ ሰንብተዋል ተብሏል፡፡


ሰሞኑን በኢራን ላይ በዛቻ ላይ ዛቻ ሲያነባብሩ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጨረሻ ከጦርነት ይልቅ ዲፕሎማሲን እመርጣለሁ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ቀውሱ አሜሪካ እና ኢራን ተስማሙ ከመባሉ ወደ ግጭት ተመለሱ በሚያሰኝ ክስተት መታጀቡን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኢራን ሹሞች የሆርሙዝ የባህር መተላለፊያ ወሽመጥ ለንግድ እና ለጭነት መርከቦች ክፍት እንዲሆን ለማስቻል የምናደርገው ንግግር ወደ መቋጫው ተቃርቧል አሉ፡፡


ወደ ማጠቃለያው ተቃርቧል የተባለው ንግግር የሚካሄደው ከኦማን ጋር ብቻ የተወሰነ እንደሆነ የኢራን ሹሞች እወቁልን ማለታቸው አልጀዚራ ፅፏል፡፡


ንግግሩ በጊዜያዊ የመርከቦች መግቢያ እና መውጫ መስመሮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


ሆኖም ኢራን በሆርሙዝ የመርከቦች ጊዜያዊ መተላለፊያ መስመሮች ጉዳይ ከኦማን ጋር ወደ ስምምነቱ ተቃርቤያለሁ ብትልም ጉዳዩ ያለቀ የደቀቀ ነው ማለት አይቻልም ተብሏል፡፡


አሜሪካ በዚህ የኢራን እና የኦማን ስምምነት ኢራን ለሆርሙዝ ተላላፊ መርከቦች ፈቃድ ሰጭ እና ነሺ መሆኗን በጭራሽ እንደማትቀበለው ተሰምቷል፡፡


በዚያ ላይ ሰባሪ ሳንቲም የአገልግሎት ክፍያ እንድትቀበል አሜሪካ እንደማትፈቅድ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


ከጦርነቱ በፊት የሆርሙዝ ወሽመጥ የአለማችን 20 በመቶ የነዳጅ አቅርቦት መተላለፊያ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡




የናይጀሪያው ፕሬዘዳንት ቦላ ቲኑቡ ለአገሪቱ የጦር ባልደረቦች የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው አዘዙ፡፡


ወታደሮች እና ባለ ዝቅተኛ ማዕረገኞቹ በመቶኛ ከፍተኛ ጭማሪ እንደተደረገላቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የእነዚህ የጦር ባልደረቦች የደሞዝ ጭማሪ 80 በመቶ እንደሚደርስ ታውቋል፡፡


ለሰራዊቱ ባልደረቦች የደሞዝ ጭማሪ እስከ ሲደረግላቸው በወር ጊዜ ውስጥ የአሁኑ 2ኛው ነው ተብሏል፡፡


ለጦር ባልደረቦቹ የደሞዝ ጭማሪ የተደረገላቸው አገሪቱ ዓይነተ ብዙ የደህንነት ፈተና በተጋረጠበት ወቅት ነው፡፡


የናይጀሪያ ጦር ከፅንፈኞች ፣ ከተደራጁ ወንበዴዎች እና ከታጠቁ አማጺያን ጋር ባልተቋረጠ ትንቅንቅ ላይ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


የደሞዝ ጭማሪው የሰራዊቱን ባልደረቦች ተልዕኮ የመፈፀም መንፈስ እንደሚያነቃቃው ተገምቷል፡፡


#ደቡብ አፍሪካ



የደቡብ አፍሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ አገራቸው በስደተኞች ጉዳይ አህጉር አቀፍ ውይይት እንዲደረግ ፍላጎት እንዳላት ተናገሩ፡፡


ላሞላ የአህጉር አቀፍ ንግግሩን ሀሳብ ያነሱት በደቡብ አፍሪካ ስደተኛ ጠል ወገኖች ሰነድ አልባ ስደተኞች ተጠራርገው ይውጡልን የሚል ግፊታቸውን በቀጠሉበት አጋጣሚ እንደሆነ አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


ስደተኛ ጠሎቹ ከጥያቄም ተሻግረው በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ፣ ድብደባ እና ዘረፋ ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡


ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ ያላቸውም አፍሪካውያን ስደተኞች ሳይቀር የጥላቻ ጥቃት ሰላባዎች እንደሆነ ይነገራል፡፡


ይህም በአህጉር ደረጃ የደቡብ አፍሪካን ገፅታ እያጠለሸው ነው ተብሏል፡፡


የደቡብ አፍሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደ ከፍተኛ የአፍሪካ ስደተኞች ተቀባይነታችን በአህጉር ደረጃ ልንነጋገርበት ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ጉዳዩ በመጪው ጥቅምት የአፍሪካ ህብረት ቅንጅታዊ ስብሰባ ወቅት አንዱ አጀንዳ እንዲሆን በጋና የቀረበው ጥያቄ ውድቅ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡




በጀርመን ምስራቃዊ ክፍል በአንድ ኤርፖርት ፈንጂ የተጫነ ሰው አልባ በራሪ አካል /ድሮን/ ተገኘ፡፡


ፈንጂ የተጫነው ድሮን የተገኘው በሌፕዚንግ ሐሌ ኤርፖርት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ኤርፖርቱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት /ኔቶ/ የወታደራዊ ጭነቶች ማስተናገጃ ጭምር ነው ተብሏል፡፡


የዩክሬይኑ አንቶኖቭ የጭነት አውሮፕላን በዚሁ ኤርፖርት እንደሚገለገል ታውቋል፡፡


በጀርመን የዩክሬይኑ አምባሳደር ፈንጁ የተጫነውን ድሮን ከሩሲያ ሌላ ማን ይልከዋል ሲሉ ሞስኮን በተጠያቂነት ከስሰዋል፡፡


ሩሲያ ግን ይሄን ጉዳይ በተመለከተ እንዲህም ነው ፤ እንዲያም ነው አላለችም፡፡


ሩሲያ እና ዩክሬይን ከ4 አመታት በላይ በጦርነት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
በአገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ ያሉ ቤተ እስራኤላውያን ከምክከሩ በኋላ እውቅና ይሰጠናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ፡፡

ነሐሴ 1 2018 በአገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ ያሉ ቤተ እስራኤላውያን ከምክከሩ በኋላ እውቅና ይሰጠናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ፡፡ በኢትዮጵያ እስከሁን ድርሶብናል ላሉት "መገለል እና መገፋት "በዓይነትም፣ በገንዘብ ካሣ እንፈልጋለን ሲሉ በኢትዮጵያ የቤተ እስራኤል የልማት ድርጅት ፕሬዚዳንት አቶ በላይነህ ታ

 
 
 
በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ማጭበርበር የተጠረጠሩ አርቲስቶች በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በከባድ ማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ወሰነ።

ነሐሴ 2018 በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ማጭበርበር የተጠረጠሩ አርቲስቶች በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በከባድ ማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ወሰነ። የተላለፈው መግለጫ ከዩቲዩብ እንዲወርድ እና ይቅርታ እንዲጠየቅ ፍርድ ቤቱ አዟል። ዐቃቤ ሕግ አርቲስቶቹ በፍርድ ቤት

 
 
 
በቅርቡ የፀደቀውን ‘‘የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ‘‘ መመሪያን ባለመተግበር ሳይበር ጥቃት በተቋሙ ላይ የአገልግሎት መቋረጥን፣ የሀገር ደህንነት ማናጋት እና በዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት ካደረሰ ሀላፊዎች ወይንም ሰራተኞች ከ7 አመት እስከ 10 አመት ፅኑ እስራት እንደሚቀጡ በአዋጁ መደንገጉ ተነገረ።

ነሐሴ 1 2018 በቅርቡ የፀደቀውን ‘‘የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ‘‘ መመሪያን ባለመተግበር ሳይበር ጥቃት በተቋሙ ላይ የአገልግሎት መቋረጥን፣ የሀገር ደህንነት ማናጋት እና በዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት ካደረሰ ሀላፊዎች ወይንም ሰራተኞች ከ7 አመት እስከ 10 አመት ፅኑ እስራት እንደሚቀጡ በአዋጁ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page