በቅርቡ የፀደቀውን ‘‘የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ‘‘ መመሪያን ባለመተግበር ሳይበር ጥቃት በተቋሙ ላይ የአገልግሎት መቋረጥን፣ የሀገር ደህንነት ማናጋት እና በዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት ካደረሰ ሀላፊዎች ወይንም ሰራተኞች ከ7 አመት እስከ 10 አመት ፅኑ እስራት እንደሚቀጡ በአዋጁ መደንገጉ ተነገረ።
- 7 hours ago
- 2 min read
ነሐሴ 1 2018
በቅርቡ የፀደቀውን ‘‘የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ‘‘ መመሪያን ባለመተግበር ሳይበር ጥቃት በተቋሙ ላይ የአገልግሎት መቋረጥን፣ የሀገር ደህንነት ማናጋት እና በዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት ካደረሰ ሀላፊዎች ወይንም ሰራተኞች ከ7 አመት እስከ 10 አመት ፅኑ እስራት እንደሚቀጡ በአዋጁ መደንገጉ ተነገረ።
የደረሰው የሳይበር ጥቃት በቸልተኝነት የተፈፀመ ስህተት ከሆነ ደግሞ በሀላፊው ወይንም በተቋሙ ሰራተኛ ከ3 እስከ 5 አመት ቀላል እስራት እንደሚቀጡ በአዋጁ ተቀምጧል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ፣ በቅርቡ የፀደቀውን “የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ ”አስመልክተው ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በማብራሪያቸው በቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ ከዚህ ቀደም የህግ ማዕቀፎች የነበሩ ቢሆንም ተጠያቂ ከማድረግ እና ተግባራዊነቱ ላይ ክፍተት በመኖሩ አስገዳጅ እና ተጠያቂነትን ያካተተው ይሄ አዋጁ እንዲወጣ አስገድዷል ብለዋል ።
በዚህም በአዋጁ የተቀመጠውን አስገዳጅ መመሪያ ባልተወጡ የቁልፍ ተቋማት ሀላፊዎች እና ሰራተኞች ላይ የአስተዳደራዊ ቅጣቶች እና የወንጀል ተጠያቂነት ማዕቀፎች ተካቷል ብለዋል።
በዚህ መሰረተ በቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የተጣለው አስገዳጅ የሳይበር ደህንነት ማዕቀፎችን በወቅቱ ባልተገበሩ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች ላይ ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ብር ቅጣት ይጣልባቸዋል ።
የሳይበር ክስተት ወይንም ጥቃት ከደረሰ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ስር ላለ የብሔራዊ አደጋ እና ክስተት ምላሽ ማዕከል በ48 ሰዓታት ውስጥ ካላሳወቁ ከ1.5 ሚሊየን እስከ 2 ሚሊየን ብር እንደሚቀጡም ተደንግጓል።
ለድንገተኛ ምላሽ ማዕከል መረጃ ወይንም ትብብር ካልሰጡ እንዲሁም ለማንኛውም የሳይበር ውይይት በራቸውን ለማይከፍቱ ተቋማት ከ300 ሺህ ብር እስከ 500 ሺህ ብር ይቀጣሉ ተብሏል።
በሌላ በኩል ለሳይበር ኦዲት ፍተሻ ትብብር የማያደርጉ ከሆነ ደግሞ ከ1.5 ሚሊዮን እስከ 2 ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚጣልባቸው ሲሆን በኦዲት ፍተሻ ከተደረገ በኋላ አሉባቸው የተባሉትን ክፍተቶች በወቅቱ ካላስተካከሉ ደግሞ ከ800 ሺህ ብር እስከ 1 ሚሊዮን ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ትዕግስት ጠቁመዋል።
ፍተሻ እና ግምገማ ያልተደረገባቸው አዳዲስ ወይንም ማሻሻያ የተደረገላቸው ሲስተሞችን ከቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጋር የማገናኘት እና የመጠቀም አዝማሚያ ካለም ከ800 ሺህ ብር እስከ 1 ሚሊዮን ብር እንደሚቀጡ በአዋጁ ተደንግጓል ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በውሳኔው ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ ከሚመለከታቸው የመንግስት እና የግል ዘርፍ የተውጣጣ ቦርድ በሚኒስትሮች ም/ቤት በደንብ እንዲቋቋም በአዋጁ መደንገጉን ወ/ሮ ትዕግስት ነግረውናል።
የተቋቋመው ቦርድም የተነሱለትን ቅሬታዎች አይቶ ቅሬታዎች ይፈታልም ተብሏል።
ነገር ግን ቦርዱ ቅሬታዬን አልፈታም፣ ፍትሕ አላገኘውም የሚል ቅሬታ አቅራቢ ሲመጣ ደግሞ በ60 ቀናት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት እንደሚችልም በአዋጁ ተደንግጓል።
አዋጁ ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት ተቋማት ራሳቸውን እንዲያደራጁ፣ የሰው ሃይል እንዲያበቁ እና ቴክኖሎጂዎቻቸውን ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲያደርጉ አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የአንድ ዓመት የቅድመ ዝግጅት ጊዜ እንደተሰጠም ሰምተናል።
ፍቅሩ አምባቸው
_edited.jpg)
