top of page

የሐምሌ 15 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

  • 9 hours ago
  • 2 min read


በሞሪታንያ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ በደረሰ የባህር አደጋ 144 ጥገኝነት ፈላጊዎቹ ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ፡፡


የአደጋው ሟቾች መነሻዋን ከጋምቢያ በማድረግ ወደ ስፔን በማምራት ላይ በነበረች ጀልባ የተሳፈሩ ጥገኝነት ፈላጊዎች እንደሆኑ አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


በጀልባዋ ተሳፍረው የነበሩት በሙሉ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ጥገኝነት ፈላጊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡


38 ጥገኝነት ፈላጊዎችን በሕይወት ማትረፍ እንደተቻለ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን /UNHCR/ መረጃ ያሳያል፡፡


አፍሪካውያን ጥገኝነት ፈላጊዎች ወደ ስፔኗ ካናሪ ደሴት በመናኛ ጀልባዎች የሚደርጉት የባህር ጉዞ አደጋ እንደሚደጋገምበት መረጃው አስታውሷል፡፡


አደጋውን ለማስቀረት ገፊ ምክንያቶቹ በወጉ ሊመረመሩ ይገባል መባሉ ተሰምቷል፡፡




የየመን ሁቲዎች የትኞቹም የመርከብ አገልግሎት ሰጭዎች መርከቦቻቸው ወደ ሳውዲ አረቢያ ወደቦች ድርሽ እንዳይሉ አስጠነቀቁ፡፡


ሁቲዎቹ ከትናንት በስቲያ የሳውዲ አረቢያን ወደቦች በሙሉ እንከረቻችምባታለን ሲሉ ዝተው እንደነበር TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡


ትናንት ደግሞ የትኞቹም መርከቦች በሳውዲ አረቢያ ወደቦች የመጫንም ሆነ የማራገፍ ተግባር እንዲያከናውኑ ከልክለናል የሚል ማስጠንቀቂያ አስከትለዋል፡፡


ትዕዛዛቸውን ለማያከብሩትም ውርድ ከራሳችን ብለዋል ሁቲዎቹ፡፡


ቀደም ሲል የኢራን አውሮፕላን በሰንዓ ኤርፖርት እንዳያርፍ ጥቃት ለመሰንዘሩ ሁቲዎቹ ሳውዲ አረቢያን በተጠያቂነት ሲከስሱ ሰንብተዋል፡፡


የኢራን የጦር አጋሮች እና የፖለቲካ ሸሪኮች መሆናቸው የሚነገረው ሁቲዎቹ ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የአገሪቱን ሰሜናዊ ክፍል ሲያስተዳድሩ በርካታ አመታት ሆኗቸዋል፡፡


በአዲሱ ፍጥጫ የየመኑ ጦርነት ሊያገረሽ ይችላል የሚለው ግምት ማየሉን መረጃው አስታውሷል፡፡




ኢራን እና አሜሪካ በጦር መጠቃቃታቸውን ቀጥለዋል ተባለ፡፡


የአሜሪካ ጦር በደቡብ እና በምዕራባዊ የኢራን ክፍሎች የሚገኝ ኢላማዎችን መደብደቡን ሬውተርስ ፅፏል፡፡


የአሜሪካ ጦር የኢራንን የጦር ማዘዣዎች እንዲሁም የሚሳየል እና የአጥቂ ሰው አልባ በራሪ አካላት /ድሮኖች/ ማስወንጨፊያዎችን ደብድቤያለሁ ብሏል፡፡


ኢራንም በባህሬን ፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሰንዘሯ ተሰምቷል፡፡


በኢራን የኤሌክትሪክ አውታሮቿ ተመትተውባታል የተባለው ኩዌት ኤሌክትሪክ በፈረቃ ለማዳረስ መገደዷን የፃፈው ደግሞ AFP ነው፡፡


ኩዌት እና ባህሬን የኢራኑ ጦርነት ካገረሸ ወዲህ የኢራን የአፀፋ ድብደባ ዋነኛ ዒላማዎች እየሆኑ መምጣታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡




አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርሃንም የመጀመሪያውን የካቢኔ ስብሰባ መምራታቸው ተሰማ፡፡


በካቢኔው ውስጥ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመባል የበቁት የኪየር ስታርመር አጋሮች የነበሩ ሹሞች አሁን እንደሌሉ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


አንዴ በርንሃም የመንግስታቸው ተቀዳሚ ተግባር የኑሮ ውድነቱን ጫና ማቅለል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


ይሄንንም ተልዕኮ አሳካዋለሁ ብለዋል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡


የሌበር የፖለቲካ ማህበሩን ዝና እና ሕዝባዊ ድጋፍ ወደነበረበት መመለሱ በአንዲት በርንሃም ትከሻ ላይ የወደቀ ሀላፊነት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ማህበሩ ድጋፍ በእጅጉ የወረደ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


በርንሃም ከፈረንሳይ እና ከዩክሬይን ፕሬዘዳንቶች እንዲሁም ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መሪዎች ጋር በስልክ መምከራቸው ተሰምቷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
ሐምሌ 7/2018 - ዓለም አቀፍ ወሬዎች

#ኢራን የኢራን አብዮታዊ ዘብ የቀድሞ አዛዥ ሆሴን ካናኒ የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ዋይት ሐውስ ድረስ ዘልቀን እንገድለዋን ሲሉ ዛቱ፡፡ ካናኒ ኢራን ደግሞ ለዚህ አቅሙም ችሎታውም አላት ማለታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡ በቅርቡ ለሟቹ የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ ስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page