ዩክሬይን ለራሷ መከላከያ የፓትሪዮት ሚሳየል እንድትሰራ የአሜሪካን ፈቃድ ልታገኝ ነው፡፡
- 1 day ago
- 2 min read
ሐምሌ 3/2018 - ዓለም አቀፍ ወሬዎች
ዩክሬይን ለራሷ መከላከያ የፓትሪዮት ሚሳየል እንድትሰራ የአሜሪካን ፈቃድ ልታገኝ ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬይን የፓትሪዮት የሚሳየል ጋሻን እንድትሰራ ፈቃድ እንደሚሰጧት መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡

ትራምፕ ዩክሬይን የሚሳየል መከላከያ ጋሻውን በራሷ እንድትሰራ የአሜሪካን ፈቃድ እንደምታገኝ ፍንጭ የሰጡት በቱርክ በተካሄደው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅ (ኔቶ) የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ ነው ተብሏል፡፡
ዩክሬይን በጦርነቱ ሂደት ይኸው የሚሳየል መከላከያ ጋሻ እንዲቀርብላት ስትጎተጉት ቆይታለች፡፡
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ሚሳየሉ በሌላ አገር መመረቱን ስታከላክል መቆየቷን መረጃው አስታውሷል፡፡
ትራምፕ ዩክሬይን የፓትሪዮት ሚሳየልን በራሷ እንድታመርት መፍቀዳቸው ከሩሲያ ጋር ከ4 ዓመታት በላይ በጦርነት ላይ ለምትገኘው አገር እንደ ልዩ እድል ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡
የሊባኖሱ ሺአ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ የአገሪቱ መንግስት ከእስራኤል ጋር የደረሰው ስምምነት በጭራሽ ስራ ላይ አይውልም አለ፡፡
ስምምነቱ በጭራሽ ተግባራዊ እንዲሆን አንፈቅድም ያሉት የቡድኑ ዋና ፀሐፊ ነይም ቃሴም እንደሆኑ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
ነይም ቃሴም የሊባኖስ መንግስት ስምምነቱን ውድቅ ሊያደርገው ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ስምምነቱ ሔዝቦላህን ጨምሮ ሁሉም መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ወገኖች ትጥቅ እንዲፈቱ ጭምር የሚጠይቅ ነው፡፡
የእስራኤል ጦር ደረጃ በደረጃ ከደቡባዊ የሊባኖስ ክፍል ሲወጣ ስፍራው በሊባኖስ ሰራዊት እንዲያዝ የሚጠይቅም አንቀፅ የተካተተበት ነው፡፡
ስምምነቱ በአሜሪካ አመቻችነት በዋሽንግተን ዲሲ መፈረሙን መረጃው አስታውሷል፡፡
ሔዝቦላህ ግን እጅ አንሰጥም እኛ ማለት እንደቀጠለ ተጠቅሷል፡፡
በሱዳኑ ጦርነት ምክንያት ወደ ግብፅ ተሰደው ከነበሩት ሱዳናውያን መካከል 800ዎቹ ወደ አገራቸው ተመለሱ ተባለ፡፡
ተመላሾቹ በ18 አውቶቡሶች በመሆን ወደ አገራቸው እንደተመለሱ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ስደተኞቹ ከግብፅ የተመለሱት የሱዳን ተስፋ በተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አነሳሽነት መሆኑ ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንትም ከ1100 በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች ከግብፅ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
ስደተኞቹ በፈቃደኝነት ከግብፅ እየተመለሱ ነው ቢባልም ለስደታቸው መንስኤ የሆነው ጦርነት ግን ከ3 አመታት በላይ ሆኖትም እንደቀጠለ ነው፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ሰፊ አካባቢን ያካለለ ጦርነት እያካሄዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በቻይና ምስራቃዊ ክፍል በሚገኝ የጫማ ፋብሪካ የደረሰ ቃጠሎ በጥቂቱ 28 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡
ቃጠሎ የደረሰበት የጫማ ፋብሪካ በፉጂኦን ከተማ የሚገኝ እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡
በአደጋው መሞታቸው ከተረጋገጠው ሌላ በርካታ ሰዎችም በቃጠሎው መውጫ ሳያጡ አልቀረም ተብሎ ተሰግቷል፡፡
የቃጠሎው ምክንያት ምን እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም፡፡
ፕሬዘዳንት ሺ ጂን ፒንግ ጉዳዩን አጣርታችሁ ተጠያቂዎቹን በአፋጣኝ ለፍትህ አቅርቡልኝ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ከወር በፊትም በቻይና ደቡባዊ ክፍል በሚገኘው ጉዋንዶንግ ከተማ በአንድ ሕንፃ ላይ ያጋጠመ የቃጠሎ አደጋ 12 ሰዎችን መግደሉን መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments