top of page

ሐምሌ 7/2018 - ዓለም አቀፍ ወሬዎች

  • 2 hours ago
  • 2 min read


የኢራን አብዮታዊ ዘብ የቀድሞ አዛዥ ሆሴን ካናኒ የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ዋይት ሐውስ ድረስ ዘልቀን እንገድለዋን ሲሉ ዛቱ፡፡


ካናኒ ኢራን ደግሞ ለዚህ አቅሙም ችሎታውም አላት ማለታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


በቅርቡ ለሟቹ የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ ስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ሲከናወን ትራምፕን የመግደል ዛቻ ሲስተጋባ ነበር ተብሏል፡፡


የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ ዓሊ ኻሚኒ ከቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር የተገደሉት በጦርነቱ መጀመሪያ አሜሪካ እና እስራኤል በፈፀሙት ጣምራ ድብደባ መሆኑ ይታወቃል፡፡


ዓሊ ኻሚኒን በመተካት ልጃቸው ሞጅታባ ኻሚኒ አዲሱ ጠቅላይ መሪ ሆነው መመረጣቸው ይታወቃል፡፡


ትራምፕ ኢራኖች እሳቸውን ለመግደል ከሞከሩ በአገሪቱ ላይ ሺህ ሚሳየሎችን አዘንብባታለሁ ሲሉ መዛታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡



ሳውዲ አረቢያ አረቢያ መራሹ የጦር ጥምረት በየመን ሁቲዎች የተተኮሱ ባልስቲክ ሚሳየሎችን አከሸፍኩ አለ፡፡


የከሸፉት የሁቲዎቹ ሚሳየሎች የተተኮሱት ወደ ደቡባዊ የሳውዲ አረቢያ ክፍል ነው መባሉን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


ቀደም ሲል ሁቲዎቹ በይዞታቸው ስር በሚገኘው የሰንዓ ኤርፖርት ላይ በጦር አውሮፕላኖች ድብደባ የፈፀመችው ሳውዲ አረቢያ ነች ቢሉም አለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግስት ጥቃቱን የፈፀምኩት እኔ ነኝ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩ ሁቲዎቹ የኢራን ወዳጆች ሲሆኑ አለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግስት ደግሞ በሳውዲ አረቢያ ይደገፋል፡፡


መቀመጫው በደቡባዊቱ የወደብ ከተማ ኤደን ነው፡፡


የተባበሩት መንግስታት የየመኖቹ ተቀናቃኞች ዳግም ወደ ጦርነት ሊመለሱ ይችላሉ በሚል ስጋት ገብቶኛል እያለ ነው፡፡


የየመን ተፋላሚዎች ከማንኛውም የሀይል ተግባር እንዲታቀቡ ተማፅኗቸዋል ተብሏል፡፡



ደቡብ አፍሪካ መንግስት ከአገሪቱ ለሚወጡ ስደተኞች አንዳችም ካሣ አልከፍልም አለ፡፡


የናይጀሪያ መንግስት በደቡብ አፍሪካ የቀጠለውን የጥላቻ ጥቃት ለመሸሽ ሐብት ንብረታቸውን ትተው ለሚወጡ ዜጎቹ ካሣ እንዲከፈላቸው ቀደም ብሎ ጥያቄ ማቅረቡን ቫንጋርድ ፅፏል፡፡


በደቡብ አፍሪካ ስደተኛ ጠል ወገኖች ሰነድ አልባ ስደተኞች ተጠራርገው ይውጡልን የሚል ግፊታቸውን ማበርታታቸው ይነገራል፡፡


ከጥያቄም አልፈው በውጭ ተወላጅ አፍሪካውያን ላይ ግድያ ፣ ዘረፋ እና ድብደባ እየፈፀሙ መሆኑ ይነገራል፡፡


በዚህ ሁኔታ በግላጭ ቁጣና ተቃውሟቸውን ካሰሙት አገራት መካከል ናይጀሪያ አንዷ ነች፡፡


የናይጀሪያ መንግስት በጥላቻ ጥቃቱ ምክንያት ከደቡብ አፍሪካ ለሚወጡ ዜጎቹ ካሣ እንዲከፈላቸው ቢጠይቅም የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለካሣ ሰባራ ሳንቲም አላወጣም ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
ኢትዮጵያ በ2018 በጀት አመት በ9 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢን አግኝታለች፡፡

ሐምሌ 7/2018 ኢትዮጵያ በ2018 በጀት አመት በ9 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢን አግኝታለች፡፡ ከውጪ አስፈላጊ ለምትላቸው እቃዎች ግዢ 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አውጥታለች፡፡ በዘጠኝ ወራቱ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከላከችው እቃ ያገኘችው ገቢና ወደ ሀገር ውስጥ ላስገባችው እቃ ያወጣች

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page