ታህሳስ 10/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 26 minutes ago
- 2 min read
ታህሳስ 10/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
አሜሪካ በተጨማሪ ሁለት አለም አቀፉ የወንጀል ችሎት (ICC) ዳኞቹ ላይ ማዕቀወብ ጣለችባቸው፡፡
ዳኞቹ ለአሜሪካ ማዕቀብ የተዳረጉት ችሎቱ እስራኤል በጋዛ ዘመቻዋ ፈፅማዋለች የተባለውን የጦር ወንጀል መመርመሩን እንዲያቆም ያቀረበችውን መሟገቻ ውድቅ በማድጋቸው ምክንያት እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ችሎቱ ቀደም ሲል በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡

በዚህም የተነሳ አሜሪካ በበርካታ የICC ዳኞች እና አቃቢያነ ህግ ላይ ማእቀብ እያከታተለችባቸው ነው፡፡
የአሜሪካ ጦር ባልደረቦች በአፍጋኒስታን አድርሰውታል የተባለን የጦር ወንጀል ለመመርመር የተነሱ የICC ባልደሮችም ለማዕቀብ መዳረጋቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
አሜሪካ እስራኤልን ከአጋርም በላይ አድርጋ እንደምትቆጥራት ይነገራል፡፡
ችሎቱ የአሜሪካን የማዕቀብ እርምጃ አለም አቀፍ ሕግን የሚፃረር ነው ብሎታል፡፡
የቤላሩሱ ፕሬዘዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አዲስ ስሪቱ የሩሲያ ኦሪሽኒክ ሚሳየል በአገራቸው መተከሉን ተናገሩ፡፡
አዲስ ስሪቱ ኦሪሺኒክ ሚሳየል ከድምፅ በእጅጉ የፈጠነ ሚሳየል እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ኦሪሽኒክን በተደጋጋሚ ሚሳየል ብሎ ዝም ነው ብለውለታል፡፡
ሚሳየሉ ከትናንት በሲቲያ አንስቶ በቤላሩስ መተከሉን ሉካሼንኮ በይፋ ተናግረዋል፡፡
ሚሳየሉ በቤላሩስ የተተከለው ሩሲያም ሆነች ቤላሩስ ከአውሮፓ ኃያላን ጋር የጦር ፍጥጫቸው በተባባሰበት ወቅት መሆኑ ታውቋል፡፡
ኦሪሽኒክ የኒኩሊየር አረርም ሊገጠምለት የሚችል ሚሳየል እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
ከ2 ወራት ገደማ በፊት ጃማይካን የመታት አውሎ ነፋስ በንብረት እና በመሰረተ ልማት ረገድ ያደረሰባት ጉዳት 15 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ተገመተ፡፡
አደጋው 45 ሰዎች መግደሉን አፍሪካ ኒውስ አስታውሷል፡፡
120 ሺህ ቤቶች እና ሕንፃዎችን ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መጉዳቱ በማጣራቱ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
በተለይም የአገሪቱ ደቡባዊ ምዕራብ ክፍል የአደጋው ዋነኛ ሰለባ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በዚሁ የአውሎ ነፋስ አደጋ ምክንያት 600 ሺህ ሰዎች አሁንም በየመጠለያው እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡
በአደጋው ምክንያት አሁንም ድረስ በርካታ አገልግሎቶች እንደተስተጓጎሉ ነው ተብሏል፡፡
ጃማይካን የመታው አውሎ ነፋስ እንደ ሔይቲ እና ኩባ ያሉ የካሪቢያን አገሮችንም ማዳረሱን መረጃው አስታውሷል፡፡
ናይጀርያ የአየር ሀይል የማጓጓዣ አውሮፕላኗ ያለ ፈቃድ በቡርኪናፋሶ በማረፉ በይፋ ይቅርታ ጠየቀች፡፡
አጋጣሚው ከተፈጠረ መሰንበቱን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
አውሮፕላኑ ያለ አንዳች ፈቃድ በቡርኪናፋሶ በማረፉ ተይዘው የነበሩ 11 የናይጀሪያ አየር ሀይል ባልደረቦች መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
አውሮፕላኑ በአስገዳጅ ሁኔታ በቡርኪናፋሶ ምዕራባዊ ክፍል ያረፈው ወደ ፖርቱጋል በማምራት ላይ በነበረበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
ናይጀሪያውያኑ አውሮፕላኑን በቡርኪናፋሶ ለማሳረፍ የተገደድነው እክል ስለገጠመው ነው ብለዋል፡፡
የቡርኪናፋሶ መንግስት ግን አውሮፕላኑ እንዲያርፍ ፈቃድ ባለመጠየቁ ክፉኛ ተቆጥቶ የውግዘት መግለጫ እስከማውጣት ደርሶ ነበር፡፡
አሁን ግን ናይጀሪያ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ አማካይነት ይቅርታ መጠየቋ ታውቋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በደቡብ አፍሪካ የኤምባሲ ባልደረቦቼ እስር እና መንገላታት አጋጥሟቸዋል በሚል ከሰሰ፡፡
የአሜሪካን ክስ ያሰሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እንደሆኑ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የማርኮ ሩቢዮ ክስ የተሰማው የደቡብ አፍሪካ መንግስት በአገሪቱ በአሜሪካ ጥገኝነት ፈላጊዎች ነች ደቡብ አፍሪካውያን ማስተባበሪያ ቢሮ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ሲሰሩ ደርሼባቸዋለሁ ያለውን 7 ኬኒያውያንን አስሮ ከአገር ማባረሩን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
ኬኒያውያኑ በቱሪስት ቪዛ ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡ እና ምንም ዓይነት የስራ ፈቃድ የሌላቸው እንደነበሩ የደቡብ አፍሪካ ሹሞች ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን የኤምባሲ ባደረቦቻችን ጭምር እስር እና መንገላታት ደርሶባቸዋል ሲሉ የደቡብ አፍሪካን መንግስት መክሰሳቸው ተሰምቷል፡፡
ሩቢዮ ይሄን ያደረጉት ይጠየቁልን ብለዋል በውግዘታቸው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የደቡብ አፍሪካን መንግስት ጥምድ አድርጎ መያዙ ይነገራል፡፡
ትራምፕም ሆኑ ሌሎች ሹሞቻቸው እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ ደቡብ አፍሪካ አሰናድታው በነበረ የቡድን 20 አባል አገሮች ጉባኤ ሳይገኙ መቅረታቸው ይታወቃል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1








