ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬይን የሰላሙን መንገድ ብትመርጥ ይሻላታል ሲሉ በድጋሚ አስጠነቀቁ፡፡
- Dec 29, 2025
- 2 min read
ታህሳስ 20/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬይን የሰላሙን መንገድ ብትመርጥ ይሻላታል ሲሉ በድጋሚ አስጠነቀቁ፡፡
የሩሲያው ታስ የወሬ ድርጅት የፑቲንን የከትናንት በስቲያ ማስጠንቀቂያ እወቁት ማለቱን የፃፈው ሬውተርስ ነው፡፡
የሩሲያ ጦር ሰሞኑን በዩክሬይን ላይ ሁለንተናዊ ጥቃቱን ማክፈቱ ይነገራል፡፡

ፑቲን የድጋሚ ማስጠንቀቂያቸው የተሰማው የሩሲያ ጦር በቅርቡ በዳኔስክ እና በዛፓሮዢያ ግዛቶች በያዛቸው ከተሞች እና አካባቢዎች ጉብኝት ያደረጉ የጦር አለቆችን ባነጋገሩበት አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ዩክሬይን ሰላሙን ካልመረጠች ለጦርነቱ ያስቀመጥነውን ግብ በጦር ሀይል ማሳካታችን አይቀርም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ጦርነቱ ያለ ሁነኛ መፍትሄ ወደ 4ኛ ዓመቱ እየታቀረበ ነው፡፡
የቻይና ሰራዊት በታይዋን ዙሪያ ገባ ታላቅ የጦር ልምምድ እያደረገ ነው ተባለ፡፡
የጦር ልምምዱ የጦር ሰራዊቱ የባህር እና የአየር ሀይሎች የተሳተፉበት ነው መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የጦር ልምምዱ በእውነተኛ ተኩስም ጭምር የታጀበ መሆኑ ታውቋል፡፡
ታይዋን ራሴን የቻልኩ ነፃ አገር ነኝ ብትልም ቻይና ግን ታይዋንን እንዳፈነገጠች ሉአላዊ የግዛት አካሏ አድርጋ ትቆጥራታለች፡፡
ቻይና ከዚህ ቀደምም በታይዋን ዙሪያ ገባ የጦር ልምምድ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
እስያዊቱ ገናና በታይዋን ዙሪያ ገባ የአሁኑን የጦር ልምምድ በማድረግ ላይ የምትገኘው አሜሪካ ለታይዋን የ11 ቢሊዮን ዶላር የዋጋ ግምት ያላቸውን ዘመን አፈራሽ የጦር መሳሪያዎችን እንደምትሸጥ እወቁልኝ ማለቷን ተከትሎ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
ኢራን 3 ሳታላይቶችን ወደ ሕዋው አመጠቀች፡፡
ትናንት ወደ ሕዋ የመጠቁት ሳታላይቶች የኢራን የመስኩ ጠበብት ውጤቶች እንደሆኑ ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡
የኢራን ሳታላይች የመጠቁት በሩሲያው ሰዩዝ ሮኬት አማካይነት ነው ተብሏል፡፡
ሁለቱ አገሮች በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ ትብብራቸው እያደገ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡
ኢራን ያመጠቀቻቸው ሳታላይቶች በግብርና ፣ በተፈጥሮ ሐብት እና በአካባቢ ጥበቃ ለታለሙ ተግባራት ማከናወኛነት የሚውሉ ናቸው ተብሏል፡፡
ኢራን እና ሩሲያ ከሕዋ ሳይንስ በተጨማሪ ሁለንተናዊ ትብብር ያላቸው አገሮች እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡
የምዕራብ አፍሪካዊቱ አገር ጊኒ ዜጎች መጪ ፕሬዘዳንታቸውን ለመምረጥ ትናንት ድምፅ ሲሰጡ ዋሉ፡፡
በጊኒ የትናንቱ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ በአገሪቱ ከ4 አመታት በፊት ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ ከተደረገ ወዲህ የመጀመሪው እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ለፕሬዘዳንታዊ ምርጫው 9 እጩዎች መቅረባቸው ታውቋል፡፡
ከእጩዎቹ መካከል የጊኒ ወታደራዊ የመንግስት ገልባጮች አለቃው ጄኔራል ማማዲ ዱንቦያ አንዱ ናቸው፡፡
ማማዲ ዱንቦያ በአሁኑ ወቅት የሽግግሩ ርዕሰ ብሔር ናቸው፡፡
በጊኒ ትናንት ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሲደረግ አገሪቱ ድንበሯን ዝግ አድርጋ መዋሏ ታውቋል፡፡
የምርጫ አከናዋኙ መስሪያ ቤት ውጤቱን በ72 ሰዓታት ጊዜ ይፋ አደርጋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1





Comments