top of page

በመምህርነት ሞያ ለሚሰለጥኑ ሁሉም መምህራን የምልክት ቋንቋ፣ የብሬል ማንበብና መጻፍ እንዲሁም የልዩ ፍላጎት ትምህርትን እንዲሰለጥኑ የሚያስገድድ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ፡፡

  • sheger1021fm
  • Nov 14, 2025
  • 2 min read

ህዳር 5 2018


በመምህርነት ሞያ ለሚሰለጥኑ ሁሉም መምህራን የምልክት ቋንቋ፣ የብሬል ማንበብና መጻፍ እንዲሁም የልዩ ፍላጎት ትምህርትን እንዲሰለጥኑ የሚያስገድድ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ፡፡


በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይኸው መመሪያ የልዩ ፍላጎት ( #አካቶ ) ትምህርት ማስፈጸሚያ መመሪያ ይሰኛል፡፡


በዚህ ባለ 25 ገጽ ረቂቅ መመሪያ መሰረት ትምህርት ሚኒስቴር በሚሰጠው የትኩረት መስክና የስልጠና ፕሮግራም ድልድልን መሰረት ያደረገ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ የምልክት ቋንቋ፣ የንግግር ወጌሻ እና የፊዚዮቴራፒ ስልጠና እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡


የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ደግሞ በመምህርነት ሞያ ለሚሰለጥኑ ሁሉም መምህራን የምልክት ቋንቋ፣ የብሬል ማንበብና መጻፍ እንዲሁም የልዩ ፍላጎት ትምህርት ማስተዋወቂያ ኮርስ በስርዓተ-ትምህርት ተካትተው እንዲሰለጥኑ ይደረጋሉ ይላል፡፡


የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢም፣ የማረፊያ ክፍል፣ የመማሪያ ክፍል፣ የመጸዳጃ ቤት፣ ቤተ-መጻህፍት፣ የዓይነስውራን ማንበቢያ ክፍል፣ ቤተ-ሙከራ እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ቢሮዎችና ማዕከሎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ እንዲሆኑ ያዝዛል፡፡

ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ መደበኛ መምህራንም የምልክት ቋንቋ፣ የብሬል ማንበብና መጻፍ፣ የዳሰሳ ምልክት ቋንቋ፣ የእንቅስቃሴና የአካባቢ ትውውቅ፣ የእለት ከእለት የኑሮ ክንዋኔዎች የክህሎት ስልጠና በሙያ ማሻሻያ መርሃ ግብር ውስጥ ተካቶ በዓመቱ መጀመሪያ ለሁለት ወራት ይሰለጥናሉ ተብሏል፡፡


በልዩ ትምህርት ቤቶች ተመድበው ለሚሰሩ ርዕሰ መምህራ እና #መምህራን የውሎ አበል እንደሚታሰብላቸው የልዩ ፍላጎት(አካቶ) ትምህርት ማስፈጸሚያ መመሪያ ደንግጓል፡፡


በልዩ ትምህርት ቤቶች፣ በልዩ ክፍሎች፣ በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ተቋማት ለሚማሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የአካል ጉዳቱ ክብደት በህክምና ማስረጃ የሚረጋገጥ ሲሆን ለእያንዳንዳቸው የማበረታቻ ክፍያ ይሰጣል ይላል፡፡


በዚህም መሰረት ለትምህርት ቁሳቁስ መግዣ በዓመት አንድ ጊዜ 1,000 ብር፣ ለደንብ ልብስ መግዣ 1,500 ብር፣ የትምህርት ቤት ምገባ በሌላቸው ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ለምግብ ፍጆታና ለትራንስፖርት ክፍያ የሚሆን ብር 1,800 ብር በየወሩ እንዲሰጣቸው ይደረጋል ብሏል፡፡


በተጨማሪም የትምህርት ቤት ምገባ ባላቸው ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ለትራንስፖርት ክፍያ የሚሆን ብር 1,000 ብር በየወሩ እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡


ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ለሚማሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ደግሞ ለቤት ኪራይ ክፍያ በየወሩ 1,500 ብር እንዲከፈላቸው ያዛል፡፡


መመርያው በስነ-አዕምሮ አሰራር ጉዳት ምክንያት በቀለም ትምህርት መዝለቅ ለማይችሉ ፍላጎትና ችሎታቸውን ያማከለ የሙያና የክህሎት ስልጠና እንዲሰጥም ይደነግጋል፡፡


የትምህርት ሚኒስቴር እነዚህን እና በርካታ ድንጋጌዎችን የያዘውን ረቂቅ መመሪያ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page