በጋምቤላ ክልል ከቀናት በፊት ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር እጃቸው አለበት የተባሉ የመንግስት አመራሮች በቁጥጥር እየዋሉ ነው ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- 1 hour ago
- 1 min read
ጥር 21/2018
በጋምቤላ ክልል ከቀናት በፊት ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር እጃቸው አለበት የተባሉ የመንግስት አመራሮች በቁጥጥር እየዋሉ ነው ተባለ፡፡
የክልሉ ሠላም አሁን ላይ በአንጻራዊነት መሻሻል ማሳየቱንም የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ነግሮናል፡፡
በጋምቤላ ክልል ከተወሰኑ ሣምንታት በፊት ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር አሁን እየተፈታ ነው ተብሏል፡፡
የክልሉ መንግስት በጊዜው ባወጣው መግለጫ የመጣውን ሰላም እና ልማት ወደ ኋላ ለመመለስ እየሰሩ ያሉ እኩይ ሀይሎች ያላቸው ወገኖች ፤ በየቦታው ሰዎች በመግደል ፤ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እና ህይወት እንዲጠፋ በማድረግ ጉዳት አድርሰዋል ማለቱ ይታወሳል።
የፀጥታ አካላትን እና አመራርን ዒላማ በማድረግ ክልሉን ወደ ለየለት የህዝቦች እልቂት ለማስገባት የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ ተስተውለዋል ሲልም በመግለጫው ጠቅሶ ነበር፡፡
አሁን ስላለው አጠቃላይ የክልሉ የሠላም ሁኔታ ዛሬ ስልክ ደውለን የጠየቅናቸው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶች ገድኮት ሠሞኑን በጋምቤላ ከተማ ከተፈጸመ ጥቃት ውጪ አጠቃላይ ሁኔታዎች ነገሮች እየተሻሻሉ ናቸው ብለውናል፡፡

የሀገር መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ፀጥታውን እየተቆጣጠሩት እንደሚገኙም ነግረውናል፡፡
ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማትም ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የነገሩን ምክትል ኮሚሽነሩ በስጋት ምክንያት ስራ ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶችም ግን አሉ ብለዋል፡፡
የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎችን አጠቃላይ ብዛት ለማወቅ ሪፖርቶች ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተሰበሰቡ እንደሆነ እና ሲጠቃለሉ እንደሚገለጹ አቶ ዶች ነግረውናል፡፡
በችግሩ ውስጥ የመንግስት አመራሮችም ተሳትፎ እንዳላቸው አረጋግጠናል ያሉት ኮሚሽነሩ በዚህ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዳሉም አክለዋል፡፡
የሠላም ችግሩን ፈጠረዋል የተባሉ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ስራ አሁንም መቀጠሉንም ምክትል ኮሚሽነሩ ነግረውናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7












Comments