top of page

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የነዳጅ ምርት መፈተሻ ላብራቶሪ ለመክፈት መሰናዳቱን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ተናገረ፡፡

  • sheger1021fm
  • 7 minutes ago
  • 1 min read

ጥር  21/2018

 

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የነዳጅ ምርት መፈተሻ ላብራቶሪ ለመክፈት መሰናዳቱን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ተናገረ፡፡

 

ከቀናት በኋላ ተመርቆ ወደ አገልግሎት ይገባል የተባለው የድርጅቱ የድሬደዋ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የነዳጅ ምርት መፈተሻ ላብራቶሪ የያዘ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡

 

በተጨማሪም የባዮ ኬሚካል እና የኤሌክትሮ መካኒካል ፍተሻ ላብራቶሪዎችን የያዘ መሆኑ ሲነገር ሰምተናል፡፡

 

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የብሔራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ከሆኑት አራት ተቋማት ውስጥ አንዱ ሲሆን የፍተሻ ስራ፣ የኢንስፔክሽን አገልግሎት እና የሰርተፍኬሽን ስራን ይከውናል፡፡

 

ከዚህ ቀደም ምርቶች ፍተሻ የሚደረግላቸው አዲስ አበባ ወደሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤት በመላክ መሆኑን ያስታወሱት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነት መዓዛ አበራ ይህንን አሰራር ለማስቀረት እና በቅርበት ክትትል ለማድረግ በክልል ከተሞች ላይ ቅርንጫፎችን እየከፈትን ነው ብለዋል፡፡

 

ከቀናት በኋላም ወደ ስራ የሚገባው የድሬደዋ ቅርንጫፍ የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ያነሱት ኢንጅነር መዓዛ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ይሁኑ አምራች ድርጅቶች በተቀላጠፈ እና ባጠረ ጊዜ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

 

ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያም ሆነ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ሲቀርቡ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እና የምርት ጥራታቸው እንዲጠበቅ እንዲህ ዓይነት ድርጅት አስፈላጊነቱ ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡

 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በመጭዎቹ አመታት በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ይህንን መሰል አገልግሎት መስጠት እንደምትጀምርም ተነግሯል፡፡

 

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት አጠቃላይ በክልል ከተሞች 9 ቅርንጫፎች እንዳሉት የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ኢንጅነር መአዛ አበራ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ አዋሳ፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ እና አዳማ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

 

ድርጅቱ ከ4 ሺህ በላይ የፍተሻ ባህሪያትን እየፈተሸ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ከ400 በላይ ምርቶችን ፍተሻ ያከናውናል ተብሎለታል።

 

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….

 

ፋሲካ ሙሉወርቅ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

YouTube : https://shorturl.at/18TS1                   

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page