top of page

ሰኔ 23 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 1 minute ago
  • 2 min read

የኢራኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መጂድ ታክት ራቫንቺ ወደ ዲፕማሲዊ ንግግር እንድንመለስ ከፈለገች አሜሪካ ተጨማሪ ጦር ጥቃት እንደማታደርስብን ማረጋገጫ ልትሰጠን ይገባል አሉ፡፡


ራቫንቺ አሜሪካ በሽምጋዮች በኩል ወደ ድርድር እንድንመለስ ጥያቄዋን አበርትታዋለች ማለታቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ከሳምንት በፊት እስራኤል በኢራን ላይ ለ12 ቀናት ከባድ ድብደባ አድርሳለች፡፡

ወደ ሁለቱ አገሮች ግጭት መቆሚያ አቅራቢያ አሜሪካም በኢራን የኒኩሊየር ተቋማት ላይ በግዙፍ ቦምቦች ጥቃት ፈፅማለች፡፡


ከዚህ በኋላ የኢራን ሹሞች ከአሜሪካ ጋር ድርድር አያሻንም ሲሉ ሰንብተዋል፡፡


አሁን ደግሞ የፋርሳዊቱ አገር ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ዳግም የጦር ድብደባ እንደማትፈፅምብን ማረጋገጫ ከሰጠች ወደ ንግግር ልንመለስ እንችላለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የኢራን የኒኩሊየር መርሐ ግብር ጉዳይ አሁንም አነጋጋሪነቱ እንዳልሰከነ መረጃው አስታውሷል፡፡



የሶሪያ መንግስት በአገሪቱ ጊዜያዊ ርዕሰ ብሔር አህመድ አል ሻራ ላይ የግድያ ሙከራ ተቃጥቶባቸው ነበር መባሉን በፍፁም ሐሰት ነው አለ፡፡


ቀደም ሲል አልሻራ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በጉብኝት ላይ በነበሩበት ወቅት የግድያ ሙከራ እንደተቃጣባቸው ወሬው ሲናፈስ መሰንበቱን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ግን ወሬው ሐሰት ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡


በአልሻራ የሚመራው የአማፂያን ጥምረት የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድን አስተዳደር በትጥቅ አመፅ ማስወገዱ ይታወቃል፡፡


አህመድ አልሻራ የቀድሞው ሥርዓት ከተወገደ በኋላ የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት ከተደረጉ ከመንፈቅ በላይ ሆኗቸዋል፡፡


ያም ሆኖ አገሪቱ አሁንም ወደ ሙሉ መረጋጋቷ እንዳልተመለሰች ይነገራል፡፡



በናይጀርያ ታዋቂው የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ሴጉን ጆርጅ ሐንካሪን በአደገኛ ዕፅ ማስተላለፍ ወንጀል ከሌሎች 4 ግብረ አበሮቹ ጋር ተያዘ ተባለ፡፡


ሐንካሪን እና ግብረ አበሮቹ የተያዙት በሌጎስ አለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል ኮኮይን የተሰኘውን ዓይነት አደገኛ ዕፅ በድብቅ ለማስገባት በሞከሩበት ወቅት ነው መባሉን ዘ ፓንች ፅፏል፡፡


800 ግራም ኮኮይን እንደተያዘባቸውም የአደገኛ እፅ ተከላካይ መስሪያ ቤቱ ሹሞች ተናግረዋል፡፡


ሐንካሪን ለብዙ ጊዜ ብራዚል ውስጥ እግር ካስ ሲጫወት ማሳለፉ ተጠቅሷል፡፡


በእሱ እና በግብረ አበሮቹ ላይ ተጨማሪ ብርቱ ምርመራ ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡



በታንዛኒያ በደረሰ ከባድ የትራፊክ አደጋ የ38 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡


38 ሰዎች ያለቁበት የትራፊክ አደጋ የደረሰው በኪሊማንጃሮ ግዛት አንድ አውቶቡስ እና ሚኒባስ በመጋጨታቸው ምክንያት እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡


በግጭቱ ወቅት በሁለቱም ተሽከርካሪዎች ላይ ቃጠሎ መቀስቀሱ ታውቋል፡፡


በቃጠሎው የተነሳ የ36 ሰዎችን አስከሬን ለመለየት አስቸግሯል ተብሏል፡፡


በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 6ቱ አሁንም በሆስፒታል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡


ግጭቱ የደረሰው የአውቶቡሱ አሽከርካሪ አውቶበሁሱን መቆጣጠር ስለተሳነው መሆኑ ታውቋል፡፡


ፕሬዘዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን እወቁልኝ ብለዋል፡፡


በታንዛኒያ ከባባድ የትራፊክ አደጋ እንደሚደጋገም መረጃው አስታውሷል፡፡


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page