top of page

መጋቢት 22/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • 1 day ago
  • 2 min read

በጀርመን ከሚኖሩ ስደተኞች 80 በመቶዎቹ ወደ አገራቸው እንደሚሸኙ መራሄ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርዝ ተናገሩ፡፡


ሶሪያውያኑ ስደተኞች በመጪዎቹ 3 አመታት ከጀርመን ወደ አገራቸው ይሸኛሉ መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


መራሄ መንግስት ሜርዝ 80 በመቶዎቹ ሶሪያውያን ስደተኞች በ3 አመታት ጊዜ ወደ አገራቸው እንደሚሸኙ እወቁልን ያሉት ከሶሪያው ጊዜያዊ ርዕሰ ብሔር አህመድ አልሻራ ጋር በበርሊን ከተነጋገሩ በኋላ ነው ተብሏል፡፡



ብዙዎቹ ሶሪያውያን ስደተኞች ጀርመን የገቡት በአገራቸው ተቀስቅሶ የነበረው ውስብስብ የእርስ በርስ ጦርነት በተፋፋመበት ወቅት ነበር፡፡


አሁን ስደተኞቹን ከጀርመን መመለስ ይጀመራል ቢባልም ዝርዝሩ ገና አልታወቀም፡፡


ሶሪያ በአሁኑ ወቅት ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው በእጅጉ የተሻለ ፀጥታ እንደሚስተዋልባት መረጃው አስታውሷል፡፡



አሜሪካ በኢራን ኢስፋሐን ከተማ በሚገኝ የከፍተኛ ጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾች ማከማቻ የምድር ውስጥ ዋሻ ላይ ከባድ የቦምብ ድብደባ መፈፀሟ ተሰማ፡፡


ማከማቻው የሚገኝበት ዋሻ በምሽግ ደርማሽ ቦምብ መመታቱን ዎል ስትሪት ጆርናል ፅፏል፡፡


የኢስፋሐኑ የታላላቅ የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ተመትቷል ስለመባሉ ከኢራን ሹሞች በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡


በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በኢራን ተተኩሷል በተባለ የሚሳየል ስብሰባሪ በ4 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡


በዛው በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የኩዌትን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ የነዳጅ መጫኛ መርከብ በኢራን ድሮን ተመትታ በእሳት ተያይዛ እንደበር ተሰምቷል፡፡


ኢራን ወደ ኢሚሬትስ ጥቃት መሰንዘሯን እንደቀጠለች ተነግሯል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ባለስልጣናት ጋር በብርቱ እየተነጋገርን ነው ቢሉም የኢራን ሹሞች ሐሰት ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡



በናይጀርያ ፕላቱ ግዛት ጆስ ከተማ ከትናንት አንስቶ የ48 ሰዓታት የሰዓት እላፊ ስራ ላይ ዋለ፡፡


በከተማዋ የ48 ሰዓታት የሰዓት እላፊ ስራ ላይ የዋለው ታጣቂዎች በአንድ መጠጥ ቤት ላይ ባደረሱት የእሩምታ ተኩስ ጥቃት 12 ሰዎችን መግደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ጥቃቱ ቀደም ሲል ተገድለዋል ለተባሉ 10 ሰዎች በቀል ነው ተብሏል፡፡


ከተማዋ ለወትሮውም ከፍተኛ የፀጥታ መደፍረስ ከሚታይባቸው አንዷ እንደሆነች ተጠቅሷል፡፡


የፕላቱ ግዛት አስተዳደር ወንጀል ፈፃሚዎቹ ተይዘው በአፋጣኝ ለህግ እንዲቀርቡ ማዘዙ ተሰምቷል፡፡


በጆስ ከተማ መጠጥ ቤት ድንገት ደራሹ ጥቃት ከመፈፀሙ አስቀድሞ በየማህበራዊ ድረ ገፅ ዛቻ ሲሰነዘር እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡



የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ በዛቻ ላይ ዛቻ እያነባበሩባት ነው፡፡


ትራምፕ ኢራን ፈጥና ካልተስማማች ሁሉንም የውሃ ማጣሪያዎቿን አወድማለሁ ማለታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


የውሃ ማጠራቀሚያዎቹ በሙሉ አይቀሩኝም ብለዋል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት፡፡


ቀደም ሲል ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝን የባህር መተላለፊያ ሰርጥ ካልከፈተች የኤሌክትሪክ አውታሮቿ አይተርፉኝም ሲሉ ሰንብተዋል፡፡


የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም ኢራን ሆርሙዝን በዚያም ሆነ በዚህ መክፈቷ አይቀርም ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡


በአንድ በኩል በኢራን ላይ ማስጠንቀቂያቸውን የሚያግተለትሉት ትራምፕ በሌላ በኩል ከኢራን ጋር የሚካሄደው ንግግር ታላቅ እርምጃ እያሳየ ነው ብለዋል፡፡


የኢራን ሹሞች ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር የተደረገ አንዳችም ንግግር የለም ሲሉ ቆይተዋል፡፡


እንደሚባለው አሜሪካ በፓኪስታን በኩል ባለ 15 ነጥቦች እቅዷን ከላከች ሰንብታለች፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
የኤሌክትሪክ ኬብሎችን የዘረፉ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ።

መጋቢት 23/2018 የኤሌክትሪክ ኬብሎችን የዘረፉ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ። ከ3.8 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኤሌክትሪክ ኬብሎችን የዘረፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አገልግሎቱ ተናግሯል። የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የደረሰው

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page