መስከረም 6 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Sep 16
- 2 min read
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ፔድሮ ሳንቼዝ እስራኤል በጋዛ በምታካሂደው የጦር ዘመቻ ተቃውሟቸውን እያበረቱት ነው ተባለ፡፡
ፔድሮ ሳንቼዝ እስራኤል የጋዛ ዘመቻዋን እንድታቆም ለማስገደድ ከማንኛውም አለም አቀፋዊ ስፖርታዊ ውድድሮች እንድትታገድ ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤል ከማንኛውም አለም አቀፋዊ ክንውን ልትታገድ ይገባል ብለዋል፡፡

ስፔን እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ ታደርሰዋለች የሚባለውን እልቂት በከፍተኛ ደረጃ ከሚያወግዙት የአውሮፓ አገሮች አንዷ ነች፡፡
ቀደም ሲልም ለፍልስጤም ነፃ አገርነት እውቅና ከሰጡት መካከል አንዷ እንደሆነች ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡
እስራኤል ዩሮ ቪዥን ከተባለው የሙዚቃ ውድድር እንድትታገድም ስፔን አቋሟን ማበርታቷ ይነገራል፡፡
የብሪታንያው ሮያል የመከላከያ ኮሌጅ ከእንግዲህ እስራኤላውያን ተማሪዎችን መቀበል አቁሜያለሁ አለ፡፡
ኮሌጁ በብሪታንያም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የመከላከያ ትምህርት ቤት እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ዝነኛው ኮሌጅ ከእንግዲህ እስራኤላውያን እጩ መኮንኖችን ተቀብዬ አላስተምርም ያለው እስራኤል በጋዛ የቀጠለችውን ከባድ የጦር ዘመቻ በመቃወም መሆኑ ታውቋል፡፡
የለንደኑ ሮያል የመከላከያ ኮሌጅ ከብሪታንያ በተጨማሪ ከ50 ያላነሱ አገሮችን እጩ መኮንኖች ተቀብሎ የሚያሰለጥን ነው ተብሏል፡፡
የጋዛ የጦር ዘመቻዋን እንድታቆም ለእስራኤል ከየአቅጣጫው የተማፅኖ ጥያቄ እየቀረበላት ነው፡፡
እስራኤል ግን የጋዛ ድብደባዋን ይበልጥ እያከፋችው መምጣቷ ይነገራል፡፡
የአሜሪካ ጦር አደገኛ ዕፅ ጭና ወደ አገሪቱ በማምራት ላይ የነበረች የተባለችን የቬኒዙዌላ አደገኛ ዕፅ አስተላላፊዎችን ጀልባ በመምታት 3ቱን ገደለ ተባለ፡፡
የቬኒዙዌላ የአደገኛ እፅ አስተላላፊዎች መገልገያ ጀልባ ነች የተባለችው ጀልባ ተመትታ መውደሟን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ መናገራቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የአሜሪካ ጦር መነሻቸውን ቬኒዙዌላ አድርገው ወደ አሜሪካ በማምራት ላይ ነበሩ ያላቸውን ጀልባዎች ሲያወድም በጥቂቱ ሳምንታት ጊዜ የአሁኗ 2ኛዋ ነች ተብሏል፡፡
በቀዳሚው ድብደባ ትራምፕ 11 የቬኒዙዌላ አደገኛ እፅ አስተላላፊዎችን ገድለናል ብለው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
ትራምፕ የቬኒዙዌላውን ፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ጭምር የአደገኛ እፅ አስተላላፊ የወንጀለኞች ቡድን አለቃ ናቸው የሚል ክሳቸውን እየደጋገሙት ነው፡፡
የቬኒዙዌላው ፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የትራምፕ አስተዳደር በአደገኛ እፅ ማስተላለፍ ጦርነት ሽፋን በአገራችን በሀይል የሥርዓት ለውጥ የማድረግ ክፉ ውጥን ይዟል እያሉ ነው፡፡
ማዱሮ አገራቸው ራሷን ለመከላከል ተገቢውን ሁሉ ታደርጋለች ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በካታር ስብሰባቸውን ያደረጉት የአረብ እና የሞስሊም አገራት እስራኤል ባለፈው ሳምንት በዶሃ የአየር ድብደባ በመፈፀሟ እርግማናቸውን አወረዱባት፡፡
የእስራኤልን የጋዛ የጦር ዘመቻም በብርቱ ቃላት እንደኮነኑት አልጀዚራ ፅፏል፡፡
እስራኤል ባለፈው ሳምንት በካታር ዶሃ የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሐማስ መሪዎች በየትኛውም ቦታ መኖሪያ ላይ ያነጣጠረ ድብደባ መፈፀሟን ራሷም ወዲያው ያልካደችው ነው፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አሸባሪ ያሏቸውን የሐማስ መሪዎች በየትኛውም ቦታ መምታት የአገራቸው መብት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዶሃ በዚሁ ጉዳይ የተሰባሰቡት የአረብ እና የሞስሊም አገሮች የእስራኤልን ድብደባ የቀጠናው የሰላም ጠንቅ ነው ብለውታል፡፡
የባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አባል አገሮችም የጋራ መከላከያቸውን ለማቀናጀት መወሰናቸው ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments