top of page

መስከረም 5 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Sep 15
  • 2 min read

የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር እስራኤል በካታር ዶሐ የፈፀመችው ጥቃት ለእኛም በጣሙን አስጊያችን ነው አለ፡፡


የቱርኩ የመከላከያ ቃል አቀባይ እስራኤል በካታር ዶሃ የሚገኘውን የሀማስ መሪዎች መኖሪያን መደብደቧን ሐላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው ብለውታል፡፡


ቀጣዮቹም የእስራኤል የጥቃት ዒላማዎች እኛ ልንሆን እንችላለን ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል የቱርኩ የመከላከያ ቃል አቀባይ፡፡

ree

ቀደም ሲል የሐማስ መሪዎችን አሸባሪዎች ሲሉ የጠሯቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የትም ይሁኑ የት ሕጋዊ ኢላማዎቻችን ናቸው ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ አስታውሷል፡፡


ቱርክም እንደ ካታር የሐማስ መሪዎች ወጣ ገባ የሚሉባት አገር እንደሆነች ይነገራል፡፡


እስራኤል ቱርክን የሐማስ ሴራ ማጠንጠኛ እና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ማዕከል ነች የሚል ክስ እንደምታሰማባት ተጠቅሷል፡፡



የቻይና ጦር ፊሊፒንስን በብርቱ ማስጠንቀቁ ተሰማ፡፡


የቻይና ማስጠንቀቂያ የተሰማው የፊሊፒንስ ጦር በደቡብ ቻይና ባህር ከአሜሪካ እና ከጃፓን ጋር ጥምር የባህር ሀይል ልምምድ ከጀመረ በኋላ እንደሆነ TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡


ቻይና በደቡብ ቻይና የባህር ወሰን እና የውሃ አካላት ይገባኛል እንደ ፊሊፒንስ ካሉ የአቅራቢያው አገሮች ጋር ውዝግቧ የቆየ ነው፡፡


ቤጂንግ የዚህ የደቡብ ቻይና ባህር አብዛኛው የኔ ነው ባይ ነች፡፡


የሶስቱ አገሮች ጥምር የባህር ሀይል ልምምድ ሲካሄድ ቻይና ደግሞ የባህር ቅኝቷን ማጠናከሯ ታውቋል፡፡


ቻይና የእነ ፊሊፒንስን ጣምራ የባህር ሀይል የጦር ልምምድ አጥብቃ መንቀፉ ተሰምቷል፡፡



የአልጀሪያው ፕሬዘዳንት አብዱልመጂድ ቴቡኔ ጊዜያዊ የነበሩትን ሲፊ ግሪየብን በቋሚ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ሾሟቸው፡፡


ግሪየብ በቋሚ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት በጊዜያዊነት ከተሰየሙ ከሳምንት በኋላ እንደሆነ ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡


ቀዳሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ናዲር ላርባዊ በምን ምክንያት ከሀላፊነት እንደተነሱ የተሰጠ ምክንያት የለም ተብሏል፡፡


ግሪየብ ቋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ካቢኔያቸውን ማደራጀት መጀመራቸው ታውቋል፡፡


በትናንትናው እለት ነባሮቹ የውጭ ጉዳይ እና የፍትህ ሚኒስተሮች ቀዳሚ ሹመታቸው ፀንቶላቸዋል ተብሏል፡፡


ሌሎችም ሚኒስትሮች እየተሾሙ መሆኑ ተሰምቷል፡፡



ሮማኒያም የአየር ክልሌ በሩሲያ ሰው አልባ በራሪ አካላት /ድሮኖች/ ተጥሶብኛል የሚል ክስ አሰማች፡፡


ቀደም ሲል ፖላንድም ተመሳሳይ ክስ ስታሰማ መሰንበቷን AFP አስታውሷል፡፡


ሮማንያም ከሩሲያ ጋር ከ3 አመት ከመንፈቅ በላይ በጦርነት ላይ የምትገኘው ዩክሬይን አዋሳኝ አገር ነች፡፡


የሮማኒያ የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በርካታ የሩሲያ ድሮኖች የአገሪቱን የአየር ክልል ጥሰው ገብተዋል የሚል መግለጫ ማውጣቱ ተጠቅሷል፡፡


የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተቃውሞውን ለማቅረብ የሩሲያውን አምባሳደር ማስጠራቱ ታውቋል፡፡


ሩሲያ እንዲህ ዓይነቱን ጠብ አጫሪነት ልታቆም ይገባል ብሏል፡፡


የሩሲያ ድሮኖች የሮማንያን የአየር ክልል ጥሰው ገብተዋል ስለመባሉ ከሞስኮ በኩል የተሰጠ አስተያየት በዘገባው አልሰፈረም፡፡


ሮማኒያም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ኔቶ/ አባል አገር ነች፡፡



በኮንጎ ኪንሻሣ ካሳይ ግዛት የኢቦላ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ፡፡


በካሳይ ግዛት ቡላፔ በተባለው አካባቢ ኢቦላ በወረርሽኝ ደረጃ መቀስቀሱ ከተነገረ መሰንበቱን አናዶሉ አስታውሷል፡፡


የተጀመረው ክትባት የወረርሽኙ መነሻ የሆነውን ስፍራ ዋነኛ ትኩረቱ በማድረግ ነው ተብሏል፡፡


በኢቦላ መከላከሉ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን አስቀድመው መውሰድ መጀመራቸው ታውቋል፡፡


በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠው ሰዎች ጋር ቅርበት ያላቸውም የክትባቱ ቅድሚያ ትኩረቱን እንዳገኙ ተጠቅሷል፡፡


በኮንጎ ኪንሻሣ ካሳይ ግዛት የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ እስካሁን የ16 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይነገራል፡፡


የአሁኑ የኢቦላ ወረርሽኝ ለኮንጎ ኪንሻሣ ባለፉት 50 አመታት ጊዜ 16ኛዋ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Recent Posts

See All
ጥቅምት 20 2018 - የፍትህ ስርዓት ችግር ምክንያት ስራው ላይ እክል እየገጠመው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ

የሚሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦች ያለ በቂ ምክንያት የማይፈፅሙ ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ቢሞክርም ባለው የፍትህ ስርዓት ችግር ምክንያት ስራው ላይ እክል እየገጠመው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ፡፡ ተቋሙ የአስተዳደር በደል ደረሰብን እምባችን ይታበስልን የሚሉ አቤት ባዮችን ቅሬታ በመቀበል

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page