መስከረም 28 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Oct 8
- 2 min read
ፖለቲካዊ ቀውሷ እየተባባሰ የመጣው የፈረንሳይ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ስልጣን እንዲለቁ እና አጣዳፊ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሊጠሩ ይገባል ተባለ፡፡
ሀሳቡን ያቀረቡት በአስተዳደራቸው የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኤድዋርድ ፊሊፕ እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ኤድዋርድ ፊሊፕ ከ5 አመታት በፊት የማክሮን አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት የፈረንሳይ መንግስት መረጋጋት ተስኖታል፡፡

በአመት ጊዜ ውስጥ በፕሬዘዳንቱ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሾም 3ኛው የሆኑት ሰባስቲያን ሌኮርኑ ወር ሳያስቆጥሩ ሀላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት ከትናንት በስቲያ ነው፡፡
በፓርላማው የማክሮን አጋር ፓርቲዎች አብላጫነታቸውን ካጡ መቆየታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
ፕሬዘዳንቱ ስልጣን ከመልቀቅ ይልቅ ፓርላማውን በትነው አጣዳፊ ምክር ቤታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ይሻሉ ተብሏል፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ማንኛውም የውጭ ጦር በጭራሽ አፍጋኒስታን ውስጥ መስፈር የለበትም አሉ፡፡
የላብሮቭ አስተያየት የተሰማው አገራቸው የአፍጋን ታሊባኖችን አስተዳደር የልዑካን ቡድን በማስተናገድ ላይ በምትገኝበት ወቅት እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በቅርቡ የአሪሜካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አፍጋኒስታኑ ባግራም የአየር ሀይል ሰፈር መመለሳችን አይቀርም ሲሉ በተደጋጋሚ መናገራቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
ፀረ ሽብር ሲል በጠራው ዘመቻ ለ20 አመታት በአፍጋኒስታን የቆየው የአሜሪካ ጦር ስትራተጂያዊነቱ የሚነገርለትን የባግራም ጦር ሰፈር ከ4 አመታት በፊት ለቅቆ የወጣው እምብዛም ባልተጠበቀ ሁኔታ ነበር፡፡
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ክስተቱን አሁን በተደጋጋሚ በቁጭት እያነሱት ነው፡፡
ሩሲያ የታሊባን አስተዳደር የውጭ ጦር በአፍጋኒስታን መስፈሩን እንዳይፈቅድ በብርቱ መጠየቋ ተሰምቷል፡፡
ሩሲያ ለአፍጋኒስታኑ የታሊባን አስተዳደር ይፋዊ እውቅና የሰጠች አገር ነች፡፡
በአሁኑ ጊዜ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እጅግ መልካም በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የታንዛኒያ ፖሊስ በአገሪቱ መንግስት ነቃፊነታቸው የሚታወቁት ሐምፍሬይ ፖሌፖሌ ታግተዋል መባሉን በብርቱ እያጣራሁት ነው አለ፡፡
ፖሌፖሌ ታግተዋል ከተባለ መሰንበቱን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
ታግተዋል የተባሉት ሐምፍሬይ ፖሌፖሌ ቀደም ሲል በኩባ የታንዛኒያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል ተብሏል፡፡
ፖሌፖሌ ከቅርብ አመታት ወዲህ በፕሬዘዳንት ሳሚያ ሱሉሁ መንግስት ላይ የሰላ ትችት ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይነገራል፡፡
ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን ከ4 አመታት በፊት ወደ ስልጣን እንደመጡ በተቃዋሚ እና ነቃፊ ፖለቲከኞች ላይ ሲደርስ የነበረውን ጭቆና አላልተውት እንደነበር ሲነገርላቸው ቆይቷል፡፡
አሁን ግን የታንዛኒያ መንግስት ተቃዋሚ እና ነቃፊዎች ወከባ እና ጭቆናው እየበረታብን ነው የሚል ምሬታቸው እንዳበዙ መረጃው አስታውሷል፡፡
#ኮንጎ ኪንሻሣ
የኮንጎ ኪንሻሣ የጦር ፍርድ ቤት ከአማጺያን ጥምረት ጋር ተባብረዋል ባላቸው 23 ግለሰቦች ላይ የእስር ቅጣት ፈረደባቸው፡፡
23ቱ ግለሰቦች ከአማጺያን ጥምረት ጋር በመተባበር ከ5 እስከ 20 አመታት የእስር ቅጣት እንደተፈረደባቸው አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
በግለሰቦቹ ላይ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸው ፍርድ ቤቱ ጥፋተኞች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ካለ በኋላ ነው፡፡
የእስር ቅጣቱ የተፈረደባቸው ግለሰቦች ADF ከተሰኘው ፅንፈኛ ቡድን ጋር ቁርኝት ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡
ADF ዋነኛ የጦር ተግባሩን የሚያከናውነው በኮንጎ ኪንሻሣ ቢሆንም መነሻ መሰረቱ ከዩጋንዳ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የኮንጎ ኪንሻሣ ምስራቃዊ ክፍል ከ100 የማያንሱ ታጣቂ እና አማጺ ቡድኖች መርመስመሻ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx












Comments