top of page

መስከረም 21፣2016-ባለንበት ወር መጀመሪያ ላይ በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውው




ባለንበት ወር መጀመሪያ ላይ በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ቢያንስ 6 ተፈናቃዮች ተገድለዋል፣ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ተናገረ፡፡


በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ፣ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት በአካባቢው የተጠለሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች መጎዳታቸው አሳሳቢ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡


ኢሰመኮ መስከረም 7፣2016 ዓ.ም. በባቢሌ አቅራቢያ በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን የተኩስ ልውውጥ በተመለከተ ተጎጂዎችን፣ የኦሮሚያ እና የሶማሊ ክልል የጸጥታ አካላትን፣ የቆሎጂ መጠለያ ሠራተኞችን እና የሆስፒታል ባለሞያዎችን ማነጋገሩን አስረድቷል፡፡


በአሁኑ ወቅት ግጭቱ ቆሟል ያለው ኢሰማኮ በተኩስ ልውውጡ ወቅት ቆሎጂ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ  ቢያንስ ስድስት  ተፈናቃዮች ተገድለዋል፣ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል እንዲሁም በሌሎች የአካባቢው ሲቪል ሰዎች ላይ  የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡


ሁለቱ ክልሎች በቅንጅት በመሥራት በአካባቢው ለተከሰተው ግጭት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች ሰላማዊ መፍትሔ በመስጠት የነዋሪዎችን እና የተፈናቃዮችን ደኅንነት በዘላቂነት የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠሩ፣ ለደረሰው ጉዳት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ባለማድረግ በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ባደረጉ የጸጥታ ኃይሎች አባላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ኢሰማኮ ጠይቋል፡፡


የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተፈጠረው ግጭት ወቅት በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረባቸው ያሉ ሲሆን  “በተለይም ቀድሞውኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ አስቸጋሪ ሕይወት ይመሩ የነበሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው አሳሳቢ ነው” ብለዋል።


ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም “በአፍሪካ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና እገዛን አስመልክቶ የተደረገው የአፍሪካ ሕብረት ስምምነት (ካምፓላ ስምምነት) መሠረት የመንግሥት የጸጥታ አካላት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የመጠለያ ጣቢያዎች ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ተግባራት ሊቆጠቡ ይገባል” ብለዋል፡፡


bottom of page